ቻምፒዮኖቹ ዝግጅታቸውን የሚጀምሩበት ቀን ታውቋል

ቻምፒዮኖቹ ዝግጅታቸውን የሚጀምሩበት ቀን ታውቋል

በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የሚመሩት ኢትዮጵያ መድኖች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሊጀምሩ ነው።

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ73 ነጥብ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ክብር ያነሱት ኢትዮጵያ መድኖች ለሚጠብቃቸው የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ እና ለሀገር ውስጥ ውድድር በቂ የመዘጋጃ ጊዜ ለማግኘት  በአዳማ ከተማ ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ።

ከክለቡ ጋር ውል ያላቸውን ተጫዋቾች አካቶ ትናንት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር አዳማ የተሰባሰበው እና ዛሬ ዝግጅቱን የሚጀምረው መድን ከክለቡ ጋር የውል ጊዜያቸው ያጠናቀቁ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾችን ውል ለማራዘም እንዲሁም አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በእንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከክለቡ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖራቸውም ስማቸውን ከበርካታ ክለቦች ጋር ሲያያዝ የነበረው አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌም በቻምፒዮኖቹ ቤት እንደሚቆዩ ተረጋግጧል።

በኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ አዘጋጅነት በመካሄድ ላይ ባለው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ሽግሽግ የተደረገበት የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ከመስከረም 9 እስከ 11 ባሉ ቀናት የመጀመርያው የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከመስከረም 16 እስከ 18 ባሉት ቀናት እንደሚከናወን ቀን ተቆርጦለታል።

ኢትዮጵያ መድንም የመጀመርያው ዙር ተጋጣሚ ቡድኑ ማን እንደሆነ ካፍ ዛሬ በካይሮ በሚያወጣው ድልድል የሚታወቅ ይሆናል።