የኢትዮጵያ መድን ተጋጣሚ ማነው?

የኢትዮጵያ መድን ተጋጣሚ ማነው?

በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ኢትዮጵያ መድንን የሚገጥመው ክለብ ሲዳሰስ…

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ኢትዮጵያ መድን የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ ኢትዮጵያን ወክሎ በአህጉራዊ መድረክ እንደሚሳተፍ ይታወቃል። ካፍ በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረገው ድልድል መሰረት ክለቡ በመጀመርያው ዙር የማጣርያ ጨዋታ የዛንዚባሩን ምላንጌን ይገጥማል።

በ 2025/26 ቶታል ኢነርጂስ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ቶታል ኢነርጂስ ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ 120 የአህጉሪቱን ክለቦች ለማሳተፍ ተዘጋጅቷል። ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሳታፍ ክለቦች ቁጥር ጨምሮ 62 ክለቦች በቻምፒየንስ ሊግ፤ 58 ክለቦች ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚያሳትፈው የካፍ የክለቦች ውድድር በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ 120 ክለቦችን ያሳትፋል።

ምላንጌ እግር ኳስ ክለብ ማነው?

ምላንጌ በዛንዚባር እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ስም ካላቸው ክለቦች አንዱ ሲሆን ከተመሰረተበት 1970 ጀምሮ የሀገሪቱን የሊግ ዋንጫ ለስምንት ጊዜያት ማንሳት የቻለ አንጋፋና ስኬታማ ክለብ ነው። በኡንጉጃ ደሴት ዛንዚባር ከተማ የተመሰረተው እና የ55 ዓመታት ታሪክ ያለው ክለቡ ከስምንት የሊግ ዋንጫዎች በተጨማሪ በሁለት አጋጣሚዎች ‘Mapinduzi Cup’ የተሰኘው የሀገር ውስጥ ውድድር ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ባለፈው የውድድር ዓመት እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ከፍተኛ ፉክክር በተደረገበት ‘PBZ’ ፕሪምየር ሊግ ተከታዩን ‘KVZ FC’ በግብ ክፍያ በልጦ በ62 ነጥቦች የሊጉን ዋንጫ በማሳካቱ ለካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ተሳትፎ የበቃ ክለብ ነው።

ክለቡ በአህጉራዊ ውድድሮች ያለው ታሪክ እና ከኢትዮጵያ ክለብ ጋር ያለው የግንኙነት ታሪክ?

ከዚህ ቀደም በአራት አህጉራዊ ውድድሮች ላይ የተሳተፈው ክለቡ በሴካፋ ክለቦች ሻምፒዮና ሦስት፤ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ የአንድ ጊዜ የተሳትፎ ታሪክ አለው። በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1994 የካቲት 18  ደግሞ በሴካፋ ካጋሜ የክለቦች ቻምፒዮና ላይ ከኢትዮጵያው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ( መብራት ኃይል)  ጋር ተጫውቶ ለኢትዮጵያው ክለብ ያሬድ ጌታቸው ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን በብቸኛው የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውም በቱኒዚያው ሴፋክስያን በድምር ውጤት ስምንት ለአንድ ተረምርሟል።

የክለቡ አሰልጣኝ?

አብዱል ሙቲክ ሀጂ ወይም በቅፅል ስማቸው ‘ኪዱ’ ከ2020 ጀምረው ቡድኑን በማሰልጠን ላይ የሚገኙ አሰልጣኝ ናቸው። ከቡድኑ ጋር የሊግ ዋንጫ ያሳኩት ወጣቱ አሰልጣኝ በሀገር ውስጥ ውድድር ጥሩ ውጤት ያላቸው ቢሆንም ክለቡን በተረከቡበት ዓመት ላይ ባደረጉት በክለቡ ታሪክ ብቸኛው የአፍሪካ መድረክ ጨዋታ በሰፊ ውጤት ተሸንፈዋል።

የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች?

የ31 ዓመቱ አብደላህ ኢዲ የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች ነው። በፊት አጥቂነት እንዲሁም በመስመር ተጫዋችነት መጫወት የሚችለው አንጋፋው ተጫዋች ባለፈው የውድድር ዓመት በ22 ጨዋታዎች 21 ግቦች እና 12 ግብ የሆኑ ኳሶች ማቀበል የቻለ ሲሆን በውድድር ዓመቱ በ33 ግቦች ተሳትፎ አድርጓል። ክለቡ የሊጉን ዋንጫ ባነሳበት ዓመት የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች የነበረው እና በ21 ግቦች የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰው ተጫዋቹ በአሁኑ ሰዓት ስሙ ‘ፓምባ ጂጂ’ ከተባለ ክለብ ጋር እየተያያዘም ይገኛል።

ክለቡ የሚጫወትበት ስታዲየም?

የታንዛኒያ ከፊል ራስ-ገዝ ክልል ተደርጋ በምትቆጠረው እና በህንድ ውቅያኖስ ውስጥ በምትገኘው ዛንዚባር ውስጥ ካሉ ሁለት ደሴቶች ውስጥ በኡንጉጃ ደሴት ዛንዚባር ከተማ የሚገኘው ‘Uwanja wa Amaan’ (Amaan Stadium) ምላንጌ ጨዋታውን የሚያደርግበት ስታዲየም ሲሆን 15,000 ደጋፊዎች የመያዝ አቅም ያለው የአርቶፊሻል ሳር የተነጠፈበት ስታዲየም ነው።