የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ድንቅ የውድድር ዓመት ያሳለፈውን የወጣቱን የመስመር ተከላካይ ውል አድሷል።
ኢትዮጵያ መድኖች በ2018 ለሚጠብቃቸው አኅጉራዊ እና ሀገራዊ ውድድር ዝግጅታቸውን በአዳማ ከተማ የጀመሩ ሲሆን ጎን ለጎን ከቡድኑ ጋር ውላቸው የተጠናቀቀውን ተጫዋቾቻቸውን ውል የማደስ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ። በትናንትናው ዕለት የቡድኑን ቁልፍ ሰው የግብዘቡን አቡበከር ኑራን ውል ያራዘሙት መድኖች አሁን ደግሞ የወጣቱን የመስመር ተከላካይ በረከት ካሌብን ውል ማራዘማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።
በሀዋሳ ከተማ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው በረከት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ያሳለፈ እና በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተጫወተ ሲሆን ባሳለፍነው የውድድር ዓመት መድንን በመቀላቀል ጥሩ የውድድር ዓመት ከማሳለፉ ባሻገር ቡድኑ ሻምፒዮን እንዲሆን ካስቻሉ ወሳኝ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆኑ ሲታወቅ በኢትዮጵያ መድን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት መስማማቱን አረጋግጠናል።