ነብሮቹ አንድ ተጫዋች ሲያስፈርሙ የተከላካያቸውን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝመዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና በተጠናቀቀው ዓመት ቡድኑን ሲመሩ ከነበሩት አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ ጋር በመለያየት በምትኩ ደግሞ ረዳት የነበሩት ካሊድ መሐመድን በአንድ ዓመት ውል በዋና አሰልጣኝነት መሾማቸው ይታወሳል። ቡድኑ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ራሱን ለማጠናከር ይረዳው ዘንድ የመስመር አጥቂውን ሲያስፈርም የተከላካዩን ውል ደግሞ ማደሱን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።
አሸናፊ ኤልያስ የክለቡ የመጀመሪያው ፈራሚ ተጫዋች ሆኗል። ከአርባምንጭ ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ በዋናው ቡድንም ጭምር መጫወት የቻለው ተጫዋቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዳማ ከተማ ከነበረው ቆይታ በኋላ ቀጣይ መዳረሻውን ሀዲያ ሆሳዕና አድርጓል።
ቡድኑ ከአዲሱ ፈራሚ ባለፈ የመሐል ተከላካዩ ዳግም ንጉሤን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሞታል።