ቻምፒዮኖቹ ውላቸው የተጠናቀቀባቸውን ተጫዋቾች ጋር ለማቆየት የሚያደርጉት ጥረት አጠናክረው በመቀጠል ሁለገቡን አጥቂ ለማቆየት ተስማምተዋል።
ኢትዮጵያ መድን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሀገሪቱን ትልቁን ዋንጫ በማንሳት ከፊቱ ለሚጠብቁት ወሳኝ ውድድሮች በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን ከመጀመሩ ጎን ለጎን ሰሞኑን በዋናነት የነባር ተጫዋቾቹን ውል እያራዘሙ መሆኑን መረጃዎችን እያደረስናቹሁ እንገኛለን።
መድኖች እስካሁን ባለው የቡድኑን አምስት ቁልፍ ተጫዋቾቸን ውል ያራዘሙ ሲሆን አሁን ደግሞ የሁለገቡን አጥቂ መሐመድ አበራን ውል ለማራዘም በክለቡ እና በተጫዋቹ በኩል ስምምነት መድረሳቸውን አረጋግጠናል።
ከሀላባ ምድር የተገኘው እና በመቻል ታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን በመጫወት መዝለቅ የቻለው በኋላም በሰበታ ከተማ፣ አዲስ አበበ ከተማ፣ በለገጣፎ የተጫወተው አጥቂው ወደ ኢትዮጵያ መድን በመምጣት ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በ24 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ አስር ጎሎችን በማስቆጠር የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ በማጠናቀቅ ቡድኑ የዋንጫውን ክበር እንዲያነሳ ትልቁን ሚና የተወጣ ተጫዋች ነበር።