ለሁለት ዓመታት አብረዋቸው የቆዩትን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ማቆየት ያልቻሉት ወላይታ ዲቻዎች ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ጋር ስማቸው የተያያዘ ሲሆን የሁለቱን አካላት አሁናዊ ሁኔታም እንደሚከተለው አጣርተናል።
በ2025 በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን የሚወክሉት ወላይታ ዲቻዎች ለሁለት ተከታታይ ዓመት ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ክለቡን በማድረስ ስኬታማ ጊዜ ያሳለፉት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ምንም እንኳን የውል ዘመናቸው ቢጠናቀቅም ዳግም ለተጨማሪ ዓመት እንዲቆዩ በሁለቱም በኩል ፍላጎት ቢኖርም ይፋዊ ባለሆነ አንድ አንድ ነገሮች ምክንያት አሰልጣኙን የማቆየት ዕቅድ ሳይሳካ ቀርቷል።
በምትኩ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር በቶሎ ወደ ማፈላለጉ የገቡት የጦና ንቦቹ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን የቡድናቸው ዋና አለቃ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለፈውን አምስት ቀናት ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም በቶሎ የአሰልጣኙን ለመቅጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ምክንያቱ ደግሞ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ከጦና ንቦቹ ጋር አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ መሆናቸውን ቢታወቅም ከቀድሞ ክለባቸው መቻል ጋር በስምምነት የተለያዩበት ጉዳይ አለመቋጨቱ እንደሆነ አውቀናል።
ታዲያ አሁን ላይ የወላይታ ድቻ እና የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የቅጥር ሁኔታ በምን ላይ ይገኛል ? ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ከመቻል ጋር ያለቸው ጉዳይ ወደ ማብቃቱ የደረሰ በመሆኑ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ነገ ቅዳሜ አሰልጣኙ ወደ ወላይታ ሶዶ በማቅናት ከክለቡ የበላይ አመራሮች ጋር ድርድር በማድረግ አብሮ ለመስራት በውስጥ ያደረጉትን ስምምነት ወደ ወረቀት በመቀየር ይፋ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሁለቱ ወገን የሚደረገው ድርድር መስመር ከያዘ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ከአምስት ዓመት በኋላ በድጋሚ ወላይታ ድቻን የሚረከቡ ይሆናል።