ቅድመ ጨዋታ | ኢትዮጵያ መድን ከ ምላንዴግ

ቅድመ ጨዋታ | ኢትዮጵያ መድን ከ ምላንዴግ

በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ኢትዮጵያን የሚወክለው ኢትዮጵያ መድን ድርጅት በነገው ዕለት የዛንዚባሩን ምላንዴግ በመግጠም ውድድሩን ይጀምራል።

በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማሸነፍ የቻለው አንጋፋው ኢትዮጵያ መድን በነገው ዕለት በታሪኩ የመጀመርያው የቻምፕዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ያደርጋል።

ነሐሴ 1 በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት እና ላለፉት አርባ አራት ቀናት በዝግጅት ላይ የቆዩት ኢትዮጵያ መድኖች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቡድኑ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ሀይደር ሸረፋ፣ መሐመድ አበራ፣ ዳዊት ተፈራ፣ አቡበከር ሳኒ እንዲሁም አዲሱ ተስፋዬ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ መስፍን ዋሼ እና አብዲሳ ጀማልን ከመሳሰሉ ተጫዋቾች ጋር በመለያየት በአዲስ ስብስብ ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

በዝውውር መስኮቱ ሙሴ ኪሮስ፣ ብሩክ ሙልጌታ፣ አማኑኤል ኤርቦ፣ ኢስማዒል አብዱልጋኒዩ፣ ማይክል ኦቶሉ እና በቃሉ አዱኛ ጨምሮ በወጣት ተጫዋቾች በተገነባ ቡድኑን ስያዘጋጁ የቆዩት የወቅቱ የሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው አመርቂ የሚባል እንዳልሆነ ጠቅሰው ዝግጅቱ ፈታኝ እንደነበረ ገልፀዋል።

አሰልጣኙ በክረምቱ ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን መልቀቃቸው ተከትሎ በአመዛኙ በመልሶ ማጥቃት የመጫወት ዝንባሌ ካለው ተጋጣሚያቸው በሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ በ2017 የውድድር ዓመት ከተከተሉት አጨዋወት የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል።

በነገው ዕለት ኢትዮጵያ መድንን ለመግጠም በዝግጅት ላይ የሚገኘው ምላንዴግ በዛንዚባር እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ስም ካላቸው ክለቦች አንዱ ነው።

ከተመሰረተበት 1970 ጀምሮ ባለፉት ሀምሳ አምስት ዓመታት የሀገሪቱን የሊግ ዋንጫ ለስምንት ጊዜያት ማንሳት የቻለው ክለቡ ከሊግ ዋንጫዎች በተጨማሪ በሁለት አጋጣሚዎች ‘Mapinduzi Cup’ የተሰኘው የሀገር ውስጥ ውድድር ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ባለፈው የውድድር ዓመት እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ከፍተኛ ፉክክር በተደረገበት ‘PBZ’ ፕሪምየር ሊግ ተከታዩን ‘KVZ FC’ በግብ ክፍያ በልጦ በ62 ነጥቦች የሊጉን ዋንጫ በማሳካቱ ለካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ ዋንጫ ተሳትፎ የበቃ ክለብ ነው።

ዝግጁትን ቀድሞ በመጀመር በቅርቡ በሲንጋዳ ብላክ ስታርስ አሸናፊነት በተጠናቀቀው ሴካፋ ካጋሜ ካፕ ላይ በሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ በአንዱ ድል ያደረገው ክለቡ በውድድሩ አምስት ግቦች አስቆጥሮ በተመሳሳይ አምስት ግቦች በማስተናገድ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ክለቡ በስብስቡ አምስት የውጭ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾት ያካተተ ሲሆን በዝውውር መስኮቱም ቪቶር ካሬ የተባለ ብራዚላዊ የተከላካይ አማካይ ከብራዚሉ ክለብ ማሞሬ፣ የመሀል ተከላካዩ ብራዚላዊው ዳቪ ከብራዚሉ ክለብ ኦፔራርዬ፣ ፈረንሳዉ አጥቂ ኤንዞ ሶቫጅ ከፈረንሳዩ ክለብ ሳፕቲመስ እንዲሁም
ኮሞሮሳዊው አማካይ ሀስላን አህመድ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ክለቦቹ በአህጉራዊ ውድድሮች ያላቸው ታሪክ

ኢትዮጵያ መድን ከዚህ ቀደም በግሪጎርያን አቆጣጠር በ1993 እና 1999 በ’ካፍ ካፕ’ እንዲሁም በ2003 በ’ካፍ ዊነርስ ካፕ’ መሳተፍ የቻለ ሲሆን በ2003 የካፍ ዊነርስ ካፕ በቅድመ ማጣርያው ራዮን ስፖርትን በድምር ውጤት ሦስት ለሁለት፣ በአንደኛው ዙር የሱዳኑን አልሜሪክ ከሜዳ ውጭ ባስቆጠረው ግብ፣ በሁለተኛው ዙር ያንግ ዋንስን በድምር ውጤት ስምንት ለአንድ፣ በሩብ ፍፃሜው ደግሞ የናይጀርያውን ዙሙንታ በድምር ውጤት ሁለት ለአንድ አሸንፎ ወደ መጨረሻዎቹ አራት ቡድኖች ውስጥ የገባው ቡድኑ በግማሽ ፍፃሜው በኮትዴቭዋሩ ስቴላ ክለብ ዲ አጃሜ ተሸንፎ ከውድድሩ የወጣበትም በክለቡ ታሪክ ምርጡ አህጉራዊ ውጤት ነው።

ከዚህ ቀደም በአንድ አጋጣሚ በአህጉራዊ ውድድር
የመሳተፍ ታሪክ ያለው የዛንዚባሩ ምላንዴግ በካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ አንድ ጊዜ ተሳትፏል። በብቸኛው የካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ ተሳትፎውም በቱኑዝያው ሴፋክስያን በድምር ውጤት ስምንት ለአንድ ተረምርሟል። በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1994፡ የካቲት 18 ደግሞ በሴካፋ ካጋሜ የክለቦች ሻምፕዮና ላይ ከኢትዮጵያው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (መብራት ሀይል) ጋር የተጫወተ ሲሆን ለኢትዮጵያው ክለብ ያሬድ ጌታቸው ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችሏል።