በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ኢትዮጵያን የወከሉት ኢትዮጵያን መድኖች የዛንዚባር አቻቸውን ምላንዴጌን 2-0 አሸንፈዋል።
በ2025/26 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ኢትዮጵያን የሚወክለው ኢትዮጵያን መድን የዛንዚባር አቻውን ምላንዴጌን ዛሬ 9:00 ሲል በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አስተናግዷል።
ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ኢትዮጵያ መድኖች በኳስ እና በእንቅስቃሴ ብልጫ በመውሰድ መጫወት የቻሉ ሲሆን በተቃራኒው ምላንዴጌዎች ከሜዳ ውጭ ከመጫወታቸው አንጻር ግብ እንዳይቆጠርባቸው በሜዳቸው በቁጥር ብልጫ በመውሰድ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ጥቅጥቅ ብለው መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው ጨዋታቸውን ቀጥለዋል።
ይህንን የመከላከል አጥር ሰብረው በመግባት ግቦችን ለማስቆጠር ያገኙትን አጋጥሚወች በተለያዩ ቦታወች ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት መድኖች 14ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል። ከግራ መስመር ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ረመዳን የሱፍ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ የወጣበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያው ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተደጋጋሚ ጫናወችን ፈጥረው ግብ ለማግኘት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት መድኖች ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 24ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የግብ ክልል በመነሳት በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ወገኔ ገዛኸኝ በግራ መስመር ያሻማውን ኳስ አጥው አማኑኤል ኤርቦ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
በአጨዋወቱ ረገድ ለውጥ ያላስመለከቱን ሲሆን ምላንዴጌኖች አሁንም መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው መጫወት የቀጠሉ ሲሆን ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው በሁልም ነገር ብልጫ በመውሰድ ግቦችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተዉሏል። በዚህም 27ኛው ደቂቃ ላይ ያረድ ካሳዬ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ የመታውን የቅጣት ምት ኳስ ግብ ጠባቂው ኡብዋ ባሮ እንደምንም ብሎ ግብ ከመሆን ታድጎታል።
ጎል አስቆጣሪው አማኑኤል ኤርቦ እና የምላንዴጉ ግብ ጠባቂ ኡብዋ ባሮ ኳስ በሚሻሙበት ወቅት ተጋጭተው ከበድ ያለ ጉዳት በማስተናገዳቸው ለተሻለ ምክምና በአምቡላንስ ወደ ግሩም ሆስፒታል ተወስደዋል።
ከዕረፍት የመልስ የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ አሁንም ኢትዮጵያ መድኖች ብልጫ የወሰዱበት ሲሆን ጫና ፈጥረው በመጫወት ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ በቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በጉዳት ተቀይሮ የወጣውን አማኑኤል ኤርቦ ተክቶ የገባው ብሩክ ሙሉጌታ የተጋጣሚ ተከላካዮችን መዘናጋት ተጠቅሞ ኳሱን አውርዶ በማረጋጋት ወደ ግብነት ቀይሮ መሪነታቸውን በሁለት ግብ ከፍ አድርጎታል።
ከረመዳን የሱፍ የሳጥን ውጭ ሙከራ በኋላ ተቀዛቅዘው የነበሩት ምላንዴጎች በመጠኑም ቢሆን ወደ ተጋጣሚ ግብ መድረስ የቻሉ ሲሆን ነገር ግን ይሄ ነው የሚባል ሙከራ አላስመለከቱንም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃዎች ሲቀሩት ብሩክ ሙሉጌታ ከራሱ ግብ በመልሶ ማጥቃት ይዞት የገባውን ኳስ ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ መድረክ ተሳትፏቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች በአማኑኤል ኤርቦ እና በብሩክ ሙሉጌታ ግቦች ታግዘው የታንዛኒያውን ምላንዴግን 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።