መቐለ 70 እንደርታዎች የአማካዩን ውል ለማራዘም ከስምምነት ደርሰዋል።
በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ ካደረጉ ክለቦች የሚጠቀሱት እና በዝውውር መስኮቱ አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም እንዲሁም የአራት ነባር ተጫዋቾች ውል ለማራዘም ከስምምነት የደረሱት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ የአማካዩ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለማራዘም ከስምምነት ደርሰዋል።
በ2017 የውድድር ዓመት በ30 ጨዋታዎች ተሳትፎ
1906′ ደቂቃዎች ቡድኑን በማገልገል ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አማካዩ ከመቐለ 70 እንደርታ ታዳጊ ቡድኑ ከወጣ በኋላ በመቻል፣ ወልዲያ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሻሸመኔ ከተማ እንዲሁም በሦስት አጋጣሚዎች በአሳዳጊ ክለቡ መቐለ 70 እንደርታ መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በክለቡ ለመቆየት ከስምምነት ደርሷል። ይህንን ተከትሎ ከኬኔዲ ገብረፃዲቅ፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ ዘረሰናይ ብርሀነ እና ሶፎንያስ ሰይፈ በመቀጠል ውሉን ለማራዘም ከስምምነት የደረሰ አምስተኛ ተጫዋች ሆናል።