ቡናማዎቹ የዓመቱን የመጀመሪያ ድል አስመዝግበዋል

ቡናማዎቹ የዓመቱን የመጀመሪያ ድል አስመዝግበዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛው ሳምንት የምድብ አንድ የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ላይ ቡናማዎቹ  ድል ሲያደርጉ አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ነጌሌ አርሲ

የሁለተኛው ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ላይ  ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻሉ በነበሩት ቡናማዎቹ በኩል በ7ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር አዳሙ ከበረከት ብርሃኑ የተቀበላትን ኳስ አክርሮ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላል። ከግቧ በኋላም በአቡበከር እና በበረከት አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በሂደት ወደ ቅኝት የገቡት ሰገኖቹም በቦና ቦካ እንዲሁም ምስጋናው መላኩ መቷት ረጂብ ሚፍታህ ከመስመር ባወጣት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ካደረጉ በኋላ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩር ገብረመስቀል ዱባለ ከምስጋናው መላኩ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች በተደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሰጎኖቹ በመልካም እንቅስቃሴ አጋማሹን ቢጀምሩም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን ቡናማዎቹ ነበሩ፤ በ51ኛው ደቂቃ በፍቃዱ ዓለማየሁ በተከላካዮች መዘናጋት ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብም በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል እንዲያሳኩ ረድታለች። ብዙም በሙከራዎች ባልታጀበው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በበረከት ወልዴ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ቢችሎም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሸገር ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በመጀመርያው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት ያስተናገዱት እና ነጥብ የተጋሩት ቡድኖች ባገናኘው ጨዋታ ላይ በመጀመርያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተመለከትንበት ነበር። በአንፃራዊነት የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ በነበራቸው ሸገር ከተማዎች በኩል ቡልቻ ሹራ ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ መናፍ ዐወል ያደረገው ሙከራም የተሻሉ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በአንፃራዊነት በሙከራም ይሁን በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ በነበረው ሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በብዙ ረገድ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። በዚህም አቡበከር ሳኒ ሳጥን ውስጥ ባደረጋት ሙከራ  እንዲሁም አሕመድ ሑሴን በአስደናቂ መንገድ ተገልብጦ የሞከራት ኳስ አዳማዎችን መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ መቀዛቀዝ በታየባቸው ሸገር ከተማዎች በኩልም ቡልቻ ሹራ፣ ያሬድ መኮንን እና ጀቤሳ ሚኤሳ ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ቀዝቃዛ የነበረው ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።