👉 ፍላጎቴ ያለንን ነገር ሁሉ ሰጥተን በታሪክ ማህደር የሚሰፍር ውጤት ማስመዝገብ ነው።
👉 ተጫዋቾቼ ማድረግ የሚገባቸውን ሁሉ በበቂ ደረጃ አድርገዋል
👉 ጨዋታው በሜዳችን ቢካሄድ ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብም እንችል ነበር ግን የሜዳ ‘አድቫንቴጅ’ አጥተንም ይህ ውጤት ማስመዝገባችን ጥሩ ነው።
በትናንትናው ዕለት በካፍ ቶታል ቻምፕዮንስ ሊግ ላይ የኢትዮጵያው ተወካይ ኢትዮጵያ መድን ከወቅቱ የውድድሩ ቻምፕዮን ፒራሚድ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ይታወሳል። በጨዋታው ዙርያ ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ቆይታ ያደረግነው ቆይታም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ጨዋታው እንዴት ነበር ?
ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ግን የገጠመን ፈተና ቀላል አልነበረም ከባድ ጨዋታ ነበር። ክለቡ የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፕዮን ነው፣ የሱፐር ካፕ ዋንጫ አሸናፊ ነው በሀገር ውስጥ ሊግ ያለው ውጤትም ጥሩ ነው። በጨዋታው የተቆጠረብን ጎል በጥሩ መንገድ የፈጠሩት ዕድል ሳይሆን በራሳችን ስህተት የተቆጠረ ነው። ከዛ ውጭም ግን ብዙ ሙከራዎች አድርገዋል ግብ ጠባቂያችን ፋሲል ገብረሚካኤልም በጣም ጥሩ ብቃት አሳይቷል፤ የሱ አስተዋጾ መግለፅም ተገቢ ነው። በአጠቃላይ ግን ጨዋታው ጠንካራ ነበር። ሁለተኛው ጨዋታም እዚ ነው የሚካሄደው ከሜዳ ውጭ ያለው ፈተና መገመት ቀላል ነው። ጨወታው በሜዳችን ቢካሄድ ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብም እንችል ነበር ግን የሜዳ ‘አድቫንቴጅ’ አጥተንም ይህ ውጤት ማስመዝገባችን ጥሩ ነው።
ለጨዋታው ስላደረጉት ዝግጅት ?
በሳውዲ ያካሄደው እንዲሁም እዚህ ግብፅ በሜዳው የአውስትራልያ ቡድንን ያሸነፈ፤ በደርሶ መልስ ኤ ፒ አርን ያሸነፈ እንዲሁም የሱፐር ካፕ ዋንጫ ያሸነፈ ቡድን ነው ጠንካራ ተጋጣሚ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን አውቀን በዛ መሰረት ባለን አቅም ራሳችንን አዘጋጅተን ነው የቀረብነው። ወሳኝ ተጫዋቾቻችን በጉዳት አጥተን ያደረግነው ጨዋታ ነበር፤ ቡድናችን ጥልቀት የለውም የተጫዋቾች ጉዳት ሲጨመርበት ደግሞ ለጨዋታዎች መዘጋጀት ከባድ ነው። እንኳን የአፍሪካ ቻምፕዮን የሆነ ቡድን በሀገር ውስጥ ውድድርም ከባድ ፈተና እንደሚገጥመን እናውቃለን። ከሀገር ውስጥ ክለቦች አንፃር ያለን የቡድን ጥልቀት እና ጥራት አይመጣጠንም ስለዚ ካለን ነገር ሲታይ ከባድ ቡድን እንደሚሆን አውቀን በጨዋታው ውጤታማ ልያደርገን የሚችል ዕቅድ አዘጋጅተን ነው የገባነው። ሆኖም ቀደም ብዬ በጠቀስኳቸው ችግሮች ውስጥ ሆነን እንዴት መጫወት እንዳለብን ባየኋቸው የተጋጣሚ የጨዋታ ቪድዮዎች ተዘጋጅተን ሁለቱን መስመሮች በመከላከል በሽግግሮች ለማጥቃት ነበር የቀረብነው መጨረሻ ላይም ተሳክቶልናል።
የወቅቱ የአህጉሩ ቻምፕዮን እንዲሁም የሱፐር ካፕ አሸናፊው ፒራሚድ እንዴት አገኛችሁት ?
አደረጃጀቱ፣ አጠቃላይ አስተዳደራዊ መዋቅሩ፣ የቴክኒክ ስታፉ እንዲሁም የቡድኑ ጥራት እና ጥልቀት ስታየው በአውሮፓ ደረጃ የሚገኝ ቡድን ነው። ጠንካራ ክለቦች አሸንፎ የመጣ ክለብ ነው። ነጥብ የጣለበት አጋጣሚ አልነበረም በአሁናዊ የፒራሚድ ብቃት ነጥብ ተጋርተን በመውጣትም የመጀመርያዎቹ ነን። በኢትዮጵያ ክለቦች ደረጃም እዚህ መጥቶ ነጥብ የተጋራ ቡድን ያለ አይመስለኝም። በጨዋታውም ጫና ፈጥረዋል። ከብራዚል፣ ሞሮኮ እንዲሁም ከግብፅ የተወጣጡ ጥሩ ስም ያላቸው ተጫዋቾች አሏቸው። የዲሞክራቲክ ሪፓፕሊክ ኮንጎ ዜግነት ያለው ተጫዋችም አላቸው ብሔራዊ ቡድን ባሰለጠንኩበት ወቅት በተካሄደ ጨዋታ እንዲሁም በትናንትናው ጨዋታ ግብ ያስቆጠረ። በጨዋታው ትኩረት አድርገንበት ነበር ግን ባገኛት አጋጣሚ አስቆጥሮብናል። በጥቅሉ ስናየው ፒራሚድ ጥሩ በሁሉም ረገድ የተሟላ ቡድን ነው በጨዋታው የገጠመን ፈተናም ከባድ ነበር።
ተጫዋቾቹ በጨዋታው ስለ ነበራቸው ብቃት ?
ተጫዋቾቼ የተሰጣቸው የጨዋታ እቅድ በትክክል ተግብረውታል ማለት ይቻላል፤ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እቅዳችን 90% ተግብረውታል። ማድረግ የሚገባቸውን ሁሉ በበቂ ደረጃ አድርገዋል። በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት ነበር፤ በማጥቃቱም በቅብብል ስህተቶች ምክንያት የተወሰኑ መቆራረጦች ነበሩ እንጂ ከዚህም በላይ ማድረግ እንችል ነበር። በአጠቃላይ ስናየው ግን እንደ ቡድን በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገናል።

ስለ ተጫዋቾች ጉዳት እና የወገኔ ገዛኸኝ ጉዳይ ?
አቡበከር ኑራ በገጠመው ጉዳት የለም፤ ወሳኙ ተጫዋቻችን ወገኔ ገዛኸኝም በጉዳት ምክንያት አልተሰለፈም አማኑኤል ኤርቦም ሙሉ ለሙሉ አገግሟል ማለት አይቻልም። ወገኔ የገጠመው ጉዳት ቀላል አይደለም ጉዳቱ ከባድ ነው። ግን ወጣት ስለሆነ በጥሩ ሁኔታ እያገገመ ነው። ስለ መሰለፉ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም በቀጣይ ቀናት ልምምዶች እናየዋለን። የብቃት ችግር የለበትም ከተሰለፈ ብዙ ነገር ያግዘናል። የፈጠራ አቅሙ ጥሩ ነው በተጨማሪም ተጫዋች የመቀነስ ብቃቱ ጥሩ ስለሆነ ተጋጣሚያችን ጫና በሚያሳድርበት ወቅት አስፈላጊ ነው። አገግሞ ከተሰለፈ አጨዋወታችን ላይ ጥሩ ለውጥ ያመጣል የሚል ዕምነት አለኝ።
በሁለተኛ ጨዋታ ከቡድንህ ምን እንጠብቅ ?
በቀጣይ ጨዋታ ምን እንደሚፈጠር መገመት ከባድ ነው። በርግጥ ተጋጣምያችን የተሰጠው ግምት እና የተመዘገበው ውጤት በተጫዋቾቻን የራስ መተማመን የሚጨምረው ነገር ይኖራል። የጥራት ልዩነት ቢኖርም እንደ ቡድን መንቀሳቀስ እንዳለብን በተጨማሪም ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ብዙ ስራዎች ሰርተን ነበር የቀረብነው፤ አሁንም በዛ መንገድ ነው የምንዘጋጀው። የባለፈው ጨዋታ ድክመቶቻችን ለማረም እንሰራለን። ለምሳሌ የሚበላሹ ኳሶች ነበሩ። ስህተቶቹ ተጋጣሚን አክብዶ በማየትና በራስ መተማመን ጉድለት የተፈጠሩ ናቸው። መዘናጋቶች እንዳይፈጠሩ ተዘጋጅተን ብንገባም ጥቂት መዘናጋቶች ነበሩ። ተጫዋቾቼ ከባለፈው ጨዋታ በተሻለ የራስ መተማመን ላይ ይገኛሉ ስለዚ ከጨዋታው የምንፈልገውን ውጤት ይዘን ለመውጣት ነው እየተዘጋጀን ያለነው። ፍላጎቴ ያለንን ነገር ሁሉ ሰጥተን በታሪክ ማህደር የሚሰፍር ውጤት ማስመዝገብ ነው።


