በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች ሐይቆቹ ወላይታ ድቻን ዐፄዎቹ ደግሞ ሲዳማ ቡናን ረተዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
በዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ መሪነት 9 ሰዓት ሲል የተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር ተደርጎበታል። 14ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ናሴሮ በድንቅ ሁኔታ ገፍቶ የወደውን ኳስ ለያሬድ ዳርዛ አቀብሎት የመስመር አጥቂው ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላም ቢሆን በተረጋጋ የኳስ ቅብብል ጨዋታውን ያስቀጠሉት ሀዋሳዎች 27ኛ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ቢኒያም በላይ በድንቅ ዕይታ ከመሃል ሜዳ የሰነጠቀለትን ኳስ ያሬድ ብሩክ በተረጋጋ አጨራረስ ግሩም ጎል አድርጎታል።
በተጫዋቾች መካከል በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ጉሽሚያዎች እና የዳኛ ፊሽካዎች ውጥረቱ እያየለ በሄደው ጨዋታ ሐይቆቹ ባልተጠበቀ አጋጣሚ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል።

የአብሥራ ደግፌ ከእጅ ውርወራ ያቀበለውን ኳስ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው ያሬድ ብሩክ በአንድ ንክኪ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ እጅግ አስደናቂ በሆነ ብቃት ኳሱን በኃይል በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ አሰልቺ ሆኖ ሲቀጥል አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግበት ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ቅብብሎች ታጅቦ በተመሳሳይ የ2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱ ለወላይታ ድቻ ሦስተኛ ተከታታይ ሽንፈት ለሀዋሳ ደግሞ ከሦስት ጨዋታ ሁለተኛ ድል አግኝቶ ነጥቡን 6 ያደረሰበት ሆኗል።
ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ
የምሽቱን መርሐግብር ዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ መርተውታል። ሆኖም ጨዋታው በጀመረ በ14ኛው ደቂቃ ዐፄዎቹ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዮሴፍ ዮሐንስ ከያሬድ ባየህ የተቀበለውን ኳስ መልሶ ለማቀበል ሲሞክር ፋሲሎች ተጭነው ኳሱን ሲቀሙት ያንኑ ኳስ እየገፋ የወሰደው በረከት ግዛው በግሩም አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት ሲዳማዎች 26ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ብርሃኑ በቀለ ራሱ ያስጀመረውን ኳስ መልሶ አግኝቶት ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖኦቲ ይዞበታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራም ግብ ጠባቂው በተመሳሳይ በቀላሉ ይዞበታል። 
ከዕረፍት መልስ በማጥቃት እንቅስቃሴው ተጠናክረው የቀረቡት ሲዳማዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ አብርዶለት ብርሃኑ በቀለ ባደረገው ሙከራ የተጋጣሚያቸውን ሳጥን ሲፈትሹ 74ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ብርሃኑ በቀለ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጨርፎበት ኳሱ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሷል። በተደጋጋሚ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሲዳማዎች 81ኛው ደቂቃ ላይም ጠንካራ ሙከራ አድርገዋል። ፈድሪክ ኑሲ ከሳጥን ጠርዝ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሞይስ በድንቅ ብቃት አስወጥቶበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በፋሲል ከነማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

