በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ድራማን ባስመለከተን ጨዋታ ነገሌ አርሲዎች ከመመራት ተነስተው አዳማ ከተማን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።
በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ለቀናት ተቋርጦ የቆየው የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከቀናት ዕረፍት በኋላ የተመለሱ ሲሆን በስድስተኛው ሳምንት መርሐግብር ቀን 10:00 ሲል አዳማ ከተማን ከ ነገሌ አርሲ ያገናኘ አገናኝቷል።

ምንም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ባላስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቢደርሱም ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን በተቃራኒው ነገሌ አርሲዎች መከላከሉ ላይ ትኩረት በሚድረግ በመልሶ ማጥቃት በከቤ ብዙነህ ተደጋጋሚ ኳሶች እና በአለኝታ ማርቆስ አማካኝነት የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ሙከራ ቢያደርጉም ኢላማቸውን መጠበቅ ተስኗቸው ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ረጅም ደቂቃዎችን ሙከራ ሳያስመለክተን የቀጠለው ጨዋታ 84ኛው ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ በጥሩ ዕይታ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን ወደ ግብነት በመቀየር አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ነገሌ አርሲዎች 90+2 ላይ ገብረመስቀል ዱባለ ያቀበለውን ኳስ ሮኅቦት ሰላሎ ከሳጥን ውጭ መትቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

የጨዋታ ሰዓቱ ተጠናቆ የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት የጨዋታ እና ስታዲየሙን ድባብ የቀየረ ግብ ነገሌ አርሲዎች ማስቆጠር ችለዋል። 90+6 ላይ ኩቤ ብዙነህ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው እና የጨዋታው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው ገብረመስቀል ዱባለ ኳስን ከመረብ ጋር በማገናኘት ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ አዳማ ከተማን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።


