ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን እና ሀዲያ ሆሳዕና አሸንፈዋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን እና ሀዲያ ሆሳዕና አሸንፈዋል

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄዱ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ2 ሲያሸንፍ ነብሮቹ ፈረሰኞቹን 1ለ0 በመርታት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ተቀዳጅተዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን

ተጠባቂው ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ እየተመራ የተካሄደ ሲሆን መድኖች ገና በ6ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ብሩክ ሙሉጌታ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው አማኑኤል ኤርቦ ግብ አድርጎታል። ቡናማዎቹ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት እያደረጉ በነበሩበት ወቅት 19ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ጎል አስተናግደዋል። ረጀብ ሚፍታህ ኳስ ሲቀበል መቆጣጠር ተስኖት በኋላም አማኑኤል ኤርቦ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን ሲገፋ ከኋላ ደርሶ ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አለን ካይዋ በግሩም መረጋጋት ከመረብ አሳርፎ የመድኖችን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

የማጥቃት ኃይላቸውን እያጠናከሩ የሄዱት መድኖች 41ኛው ደቂቃ ላይም ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ብሩክ ሙሉጌታ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ቡናማዎቹ 65ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ጎል አግኝተዋል። ሳጥን ውስጥ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ካደረጉ በኋላ ኳሱን ያገኘው በፍቃዱ ዓለማየሁ በድንቅ ምት ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል።

ቡናማዎቹ በሚያገኟቸው ኳሶች ሁሉ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በማድረግ ተጭነው መጫወታቸውን ሲቀጥሉ በስተመጨረሻም 84ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ታደሰ ከሚኪያስ በዳሶ የተቀበለውን ኳስ ከረጅም ርቀት እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ አስቆጥሮታል። ከዚህ ጎል በኋላም ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች ሳይደረጉ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ መሪነት የተጀመረ ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ከነበረው ፉክክር ውጪ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩበትም ነበር። ሆኖም ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ቀዝቃዛ በነበረው ጨዋታ ነብሮቹ 41ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የፈረሰኞቹ ተከላካዮች ኳስ ወደ ግብ ጠባቂያቸው በግንባር ገጭተው ለማቀበል ሲሞክሩ ብሩክ በየነ በፍጥነት ደርሶ ግብ ጠባቂውን ማለፍ ሲችል ግብ ጠባቂው ሻሂኪሎ ፋርክ በሠራበት ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ብሩክ ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ በጥሩ እንቅስቃሴ የተመለሱት ጊዮርጊሶች በተለይም 58ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያዎች ሳጥን ውስጥ ካገኙት ሁለተኛ ቅጣት ምት የቀሙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ወስደው ሳይጠቀሙበት የቀረው አጋጣሚ የሚጠቀስ ሲሆን 72ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከማዕዘን በተሻማለት ኳስ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል የወጣበት ኳስ የቡድኑ ለግብ የቀረበው የተሻለ ሙከራ ነበር። ጨዋታውም በተመሳሳይ ሂደት ቀጥሎ በሀዲያ ሆሳዕና 1ለ0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ድሉ ለነብሮቹ በውድድር ዓመቱ የተገኘ የመጀመሪያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።