ዛሬም በተካሄዱት ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ቡናማዎቹ እና ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ማሸነፍ ችለዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በኳሱ ቁጥጥሩ ረገድ ተመጣጣኝ የተባለ እንቅስቃሴን ያስመለከቱን ሁለቱም ቡድኖች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሶ የግብ ሙከራዎችን በመሞከር ረገድ በሁለቱም ቡድን በኩል ክፍተቶች የነበሩ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አቤል ሀብታሙ ከሀሰን ሁሴን የተቀበለውን ኳስ አመቺ ሁኔታ ላይ ሁኖ ቢያገኘውም በማይታመን ሁኔታ ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጥቶበታል ይህም በአጋማሹ የተመዘገበ ብቸኛ የግብ ሙከራ ሁኖ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 59ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሻሂክሎ ፋርክ ኳሱን ከግቡ ለማራቅ ሲል በሰራው ስህተት ሀሰን ሁሴን ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከተቆጠረው ግብ በስተቀር ይሄ ነው የሚባል ሌሎች የግብ ሙከራዎችን ሳያስመለክተን ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሸገር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በጅማሮው ግብን ባስመለከተን በማታው ጨዋታ 4ኛው ደቂቃ ላይ አሚር አብዶ በሜዳው የቀኝ ክፍል ተከላካዮችን አታሎ ያሻማውን ኳስ ጀቤሳ ሜኤሳ በግንባሩ በመግጨት ግብን አስቆጥሮ ቡድኑን ገና በጅማሮ መሪ ማድረግ ችሏል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ ከረጅም ርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ባህሩ ነገሽ ደካማ የሆነ ውሳኔ ቢወስንም ኳሷ በግቡ ቋሚ ለጥቂት ወጥታለች። ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ቡናማዎቹ 36ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ ከሳጥን ውጭ የመታውን ኳስ ራምኬል ጀምስ የኳሱን አቅጣጫ በመቀየር ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን ሸገር ከተማዎች በቾል ላም እንዲሁም ቡናማዎቹ በተመስገን ታደሰ የቅጣት ምት ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን 59ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ቅርፅ የቀየረ አጋጣሚ ተፈጥሯል፤ የሸገር ከተማው ተጫዋች ፍቅሩ ዓለማየሁ የሠራውን ጥፋት ተከትሎ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ ሲሆን ይህንን የቁጥር ብልጫ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ጫናን መፍጠር የቻሉት ቡናማዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ የሸገር ከተማ ተጫዋች ሳጥን ውስጥ ራምኬል ጀምስ ላይ የሠሩትን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት አቡበከር አዳሙ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ቡናማዎችም ከመመራት ተነስተው ሸገር ከተማን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።


