በሳሙኤል ስለሺ
ጀርመን ስፖርት ዩኒቨርሲቲ- ኮሎን
እንደ አለመታደል ሆኖ ባለሙያን ህያው ሳለ የማክበር እና ስለ እርሱ የመመስከር ልማዳችን እምብዛም ነው። አንድ ሰው አልጋ ካልያዘ አለፍ ሲልም እስትንፋሱ ካልተቋረጠ በስተቀር ስለሰው መልካም መናገር ከአድር ባይነት እና ከጥቅመኝነት ጋር አብዝቶ ይያያዛል። ባለሙያን በሀገሩ ማሳደድ ከሀገር ሲወጣ አልያም ሲሰደድ ደግሞ መናፈቅ ስሪታችን እስኪመስል ተዋህዶናል።
ሰሞኑን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ መነጋገሪያ ከሆኑ አጀንዳዎች መሀከል አንዱ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ ላይቤሪያ መሄድ ነው፡፡ አሰልጣኙን በቅርበት እንደሚያውቀው፣ አብሮት እንደሰራ የሙያ አጋሩ እና የኢትዮጵያን እግር ኳስ በጥልቀት እንደሚከታተል ባለሙያ በዚህ ስደት ላይ በጊዜ እና በሂደት ፋይዳ የሚኖረው ነገር መፃፍ እንደሚገባኝ ስለተሰማኝ ይህንን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ አንባብያን እና ለእግር ኳሱ ቤተሰቦች ለማድረስ ወደድሁ፡፡ ፅሁፉ ሶስት መሰረታዊ ክፍሎች ሲኖሩት የመጀመሪያው አሰልጣኝ ውበቱን በማውቀው ደረጃ እና በገባኝ ልክ የገለፅኩበት፥ ሁለተኛው አጭር የብሄራዊ ቡድኑን ቆይታ ውጤት ያስቀመጥኩበት ሲሆን ዋንኛው እና ሶስተኛው ደግሞ አሰልጣኙ በሁለት አመት ከግማሽ የብሄራዊ ቡድኑ ቆይታው የደረሰበትን ኢ-ስፖርታዊ ጫና እና ሆነ ተብሎ ጉዳት ለማድረስ የተሰሩበትን ዘገባዎች ይዳስሳል።
ውበቱን ሳውቀው
በሐዋሳ ከተማ በነበረኝ አጭር የህይወት ቆይታ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚያዝናኑኝ ነገሮች አንዱ የውበቱ አባተ ሐዋሳ ከተማ ነበር፡፡ በእዛ ሰው ሰራሽ እና ምቹ ሜዳ ላይ ታፈሰን ሲቦርቅ መመልከት፣ ከጋዲሳ ረዣዥም ኳሶች ጋር አይንን ወዲያ እና ወዲህ ማድረግ፣ የዳንኤል ደርቤን ኦቨር ላፕ ማየት፣ የጣቁሩ፣ አባትን እና ሌሎች እንቅስቃሴን መመልከት ደስ የሚያሰኝ ሲሆን አስጨፋሪዎቹ ቢኒ ዳና እና ታሪኩ ከነበሩ ደግሞ የተለየ የእረፍት ቀን ስሜት ይፈጥር ነበር፡፡ ምንም እንኳን ቡድኑ ከሜዳ ውጭ በሚያስመዘግበው ዝቅተኛ ውጤት ምክንያት ወደ ኋላ ቢቀርም ሜዳው ላይ ተጋጣሚዎቹን የሚያንበረክክበት መንገድ እኔ ከምወደው የጨዋታ ዘይቤ ጋር ስለሚመሳሰል የአሰልጣኙ አድናቂ ለመሆን ቻልኩ፡፡ አልፎ አልፎም በቆመበት ቴክኒካል ኤሪያ የሚያሳየው ቁንጥንጥ ባህሪው ለኳሱ ያለውን ፍቅር እና ማስመሰል የማይችል ሰው እንደሆነ አድርጌ ልረዳው በቃሁ፡፡ (እንደ ባለሙያ ማን እየሰራ ማን እያስመሰለ እንደሆነ ለመረዳት የሚቸግረኝ ሰው አይደለሁም፤ ብዙ ወሳኝ ነጥቦች (Cues) ማንበብ እችላለሁ)
አልፎ አልፎም በዩኒቨርስቲያችን ሜዳ ላይ ልምምድ ያደርጉ ስለነበር ከጨዋታው በዘለለ ስልጠናውንም የመከታተል እድል አግኝቼ ነበር፡፡ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች በተጨማሪ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምዘናና የልኬት ተግባራትን ያከናውን ስለነበር ፊቱ ብሩህ የሆነ ለዘመናዊነት እና ለእውቀት ቦታ የሰጠ አሰልጣኝ እንደሆነ አድርጌ አስብ ነበር።
የፊት ለፊት ትውውቃችን የጀመረው በኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ላይ ተባባሪ አዘጋጅ በመሆን ሳገለግል እንግዳ ሆኖ በፕሮግራማችን ላይ ከቀረበ በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ ማንቸስተር ሲቲ እና ጋርዲዮላ ላይ ያተኮረውን ተከታታይ ፊልም መሰረት አድርገን ስለ ሀገራችን አሰልጣኞች ብቃት እና የልማት ስራዎች ብዙ ተወያይተን አስተማሪ ሀሳቦችን ለተመልካቾቻችን ለማድረስ ችለን ነበር፡፡
ይህ ከሆነ ከወራት በኋላ ኢንስትራክተር አብርሀም መብርኸቱ ከብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ተነስቶ (ኮንትራቱ አልቋል በሚል) በምትኩ ውበቱ አባተ እንዲተካ የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም በዚሁ የእግር ኳስ ልሳን በሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ ላይ አስተያየቴን ሰጠሁኝ፡፡ አብርሀም የጀመረውን ስራ እንዲቀጥል፣ ከኮትዲቮር ጋር ያሳየው እንቅስቃሴ አመርቂ በመሆኑ ኮንትራቱ ቢጠናቀቅም ተጨማሪ እድል እንዲሰጠው፣ ከኮቪድ መልስ ቡድኑ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ስለማይታወቅ ከአዲስ አሰልጣኝ ይልቅ እራሱ አብረሀም ቢይዘው እንደሚሻል በመጠቆም የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተቃውሜ፤ የውበቱን መቀጠር ነቅፌ፥ የቴክኒክ ኮሚቴውን ምክረ ሀሳብ ደግፌ በግልፅ አስተያየቴን ሰጠሁ፡፡
ይህ አስተያየት በሶከር ኢትዮጵያ ላይ በይፋ ከወጣ ከቀናት በኋላ ግን ውበቱ አባተ ወደ ስልኬ ደወለ፡፡ በአስተያየቴ ቅር እንደተሰኘብኝ እያሰብኩ እና እንዳልተረዳኝ እያሰላሰልኩ ስልኩን አንስቼ አወራሁት፡፡ እርሱ ግን “አብረን ምን መስራት እንችላለን? አብረን እንድንሰራ እፈልጋለሁ” ከሚል ቀጥተኛ የእንተጋገዝ ጥያቄ ውጭ በአስተያየቴ እንዳልተከፋ እና የተናገርኩትን እርሱም የሚያምንበት እንደሆነ ነግሮኝ “የምታስበውን ነገር እንኳን እኔ ያሳደጉህ ቤተሰቦችህ እንኳን ሊቆጣጠሩት አይችሉም” ሲል የሀሳብ ነፃነት ላይ ያለውን አመለካካት ገለፀልኝ፡፡
ይህንን የምፅፈው የእኔ እና የእርሱ ግኑኝነት የአንባቢው እና የስፖርት ቤተሰቡ ራስ ምታት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሰረታዊ ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን ትውውቃችን ከዘር፣ ከሀይማኖት፣ ከጥቅም፣ ከእከክልኝ ልከክልህ የፀዳ እና ሙያዊ ብቻ እንደሆነ ታውቆ አጠቃላይ ፅሁፌ ተአማኒነቱ እንዲጨምር ለማስቻል ነው፡፡
ውበቱ ከ12ኛ ክፍል የዘለለ ትምህርት ያለው አይመስለኝም፤ ሆኖም ግን ተምረናል ከምንል እኔን መሰል ባለሙያዎች የተሻለ የስፖርት ሳይንስ አረዳድ አስተውዬበታለሁ። የውጭ ቋንቋ አጠቃቀሙም ቢሆን እራሱን በምን ያህል መጠን እንደሚያስተምር ማሳያ ነው፤ ቴክኖሎጂን የመረዳት እና በልኩ የመጠቀም ችሎታውም ኳሱ ውስጥ ባሉ ሰዎች በብዛት የማይታይ ነው፡፡ ከአካል ብቃት ባለሙያው የሚሰጠውን አህዛዊ መረጃዎች፣ ሰንጠረዦችን እና ግራፎችን የሚያነብበት እና ጥቅል መረጃ የሚወስድበት መንገድ ዘወትር ያስገርመኝ ነበር። አዳዲስ ሀሳብ ለመቀበል፣ ለመከራከር፣ ለመወያየት ያለው ቦታ እጅግ የጎላ ነው፡፡ የስእል እና የሙዚቃ ተሰጥኦ ባለቤት መሆኑ የአድማሱን ስፋት ይመሰክራል፡፡ አብረን በቆየንባቸው አጭር ጊዜያት ውስጥ ደግሞ ከሸር፣ ከአሉባልታ፣ ከነገር የፀዳ ሰው እንደነበር ለማየት ችያለሁ፡፡ ጀማሪ እና ተሸሽገው ለቀሩ ባለሙያዎች እድል በመፍጠሩ ረገድ እኔ፣ የቪዲዮ አናሊስቱ፣ የስነ ምግብ ባለሙያው፣ የግብ ጠባቂዎቹ አሰልጣኝ ጥሩ ማሳያ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ፡፡ እዚህ ጋር የኢንስትራክተር አብርሀምንም ሚና ማስታወስ ተገቢ ነው።
ውበቱ በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ እንደማንኛውም የሰፈር አሰልጣኝ ኳስ በኬሻ ተሸክሞ የአዳማ ህፃናትን የሚያሰለጥን አሰልጣኝ እንደነበር አጫውቶኛል፡፡ ዛሬ የለበሰውን የብሄራዊ ቡድን መለያ ከመልበሱ በፊት አፈር የቃሙ ብዙ ካኒቴራዎች ነበሩት፤ እዚህ ለመድረስ የሄደበት እርቀት በእርሱ አንደበት ሲነገሩ አጀብ የሚያሰኙ ናቸው፡፡ የተቀደደ ኳስ ከባለቤቱ ጋር እየሰፋ የአሰልጣኝነትን መሰላል የወጣ ባለሙያ ነው። እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት በባህር ሀገር አቋርጦ እስከመሰደድም ደርሶ ነበር፡፡ አሰልጣኙ ይሄንን ሁሉ ውጣ ውረድ ችሎ እራሱን እያስተማረ እና እየደገፈ ለብሄራዊ ቡድኑ ሲበቃ ግን በኢ-ፍትሀዊነት ስራውን ለማስጣል እና እንጀራውን ለማሻገት ደፋ ቀና ያሉ ብዙ እንደሆኑ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡
ውበቱ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
ውበቱ በብሄራዊ ቡድኑ ቆይታ ጥሩ ስራ ሰርቷል ብለው ከሚከራከሩት ወገን ነኝ፤ ሆኖም ግን በአሰልጣኙ ላይ ካለኝ መልካም ስሜት አንፃር የውበቱን የብሄራዊ ቡድን ግምገማ አንባቢን የሚያሳስት፣ የሶከር ኢትዮጵያን ቤተሰቦች የሚያታልል እንዳይሆን በማሰብ ከአኃዛዊ መረጃዎች ውጭ በጥልቀት ገብቼ ስለ ታክቲክ፥ ቴክኒክ፥ የኳስ ቁጥጥር ወዘተ ለመተንተን አልፈልግም፡፡
ውበቱ አባተ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት 24 ኦፊሴላዊ ጨዋታዎችን አድርጎ 24 ነጥቦችን ሰብስቧል፤ በዚህም ሂደት 26 ጎሎችን አስቆጥሮ 28 ግቦች ተቆጥረውበታል። ይህንን አኀዝ ከእርሱ በፊት ከነበሩ 48 ጨዋታዎች ጋር ማወዳደር እና ከእርሱ በኋላ ከተደረጉ 24 ጨዋታዎች ጋር በማነፃፀር ጥልቀት ያለው ትንታኔ በማቅረብ የእርሱን ቡድን ጥንካሬ እና ድክመት አውጥቶ ማሳየት ይቻላል። ሆኖም ግን የዚህ ፅሁፍ አላማ ይህ ባለመሆኑ እና የ96 ጨዋታዎች (የ12 አመት) የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች በፌዴሬሸኑ የቴክኒክ ክፍል በኩል በጥልቀት ቢተነተን መልካም ነው በማለት ጥቆማ በመስጠት ብቻ አልፈዋለሁ።
ውበቱ ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች መሀከል በሜዳው ያደረገው 4 ብቻ ሲሆን 3ቱን ለማሸነፍ ችሏል፤ ከመሀከለኛው እና ምስራቅ አፍሪካ ቡድኖች ጋር ለመጫወት የቻለው በአራት አጋጣሚ ብቻ ሲሆን ከደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ አድርጓል። በወቅቱ የፊፋ ደረጃ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚያንስ ቡድን የገጠመው ሁለቴ ደቡብ ሱዳንን ሲሆን ደረጃቸው ከ100 በታች የሆኑ ጠንካራ የአፍሪካ ሀገራትን ደግሞ 12 ጊዜ ለመፋለም ተገዷል፤ ጋና፣ ካሜሮን፣ አይቮሪኮስት፥ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኬፕቨርዴ ከእነዚህ መሀከል ይገኛሉ።
በአጠቃላይ ውበቱ ከሜዳው ውጭ እየተጫወተ፤ ከምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ጋር እምብዛም ሳይገናኝ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ታላላቅ የአፍሪካ ቡድኖች ገጥሞ ያስመዘገበው ውጤት በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ደረጃ እና ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መጥፎ የሚባል አይደለም።
«ጦር ከፈታው – ወሬ የፈታው»
ውበቱ ከላይ ባስቀመጥኩት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ነባራዊ የእግር ኳስ ደረጃ እና ሁኔታ አንፃር መጥፎ ውጤት ባያስመዘግብም የተወራበት አሉባልታ እና የተሰነዘረበት ነቀፌታ ግን ርዕት (Fairness) የጎደለው ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ እና ካለበት ሁኔታ አንፃር የሚቻለውን ቢያደርገም ስር የሰደደ ጥላቻ፣ ነቀፌታ እና ከወትሮው የተለየ ስም ማጥፋት በሚዲያ ተሰንዝሮበታል የሚል ምልከታ አለኝ። አብዛኞቹ በስመ ሽምግልና ይቅርታ የተጠያየቀባቸው እና እርቅ ያወረደባቸው ጉዳዮች በመሆናቸው እንዲህ እንደዛ እያሉ ማውራቱ አስፈላጊ ባይሆንም ጉዳዩ ከውበቱ በላይ የሀገርም፥ የሙያም ስለሆነ በአስተማሪነት ማንሳቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።
ከውበቱ ጋር በብሄራዊ ቡድን አብሮ እንደሰራ እና በቅርበት እንደሚያገኘው የስራ ባልደረባ በእነዛ ሁለት አመት ከግማሽ ውስጥ በሜዳ ላይ ካጋጠመው ጫና ይልቅ ከሜዳ ውጭ የደረሰበት ግፊት የበለጠ ገዝፎ ይሰማው እንደነበር አምናለሁ፡፡ የአንድን ሐገር ብሄራዊ ቡድን እያሰለጠነ፣ ባሸነፈ ቁጥር እየተሸለመ፣ ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈለው “ከግፊት እና ከጫና ውጭ ሊሆን አይችልምም፤ አይገባምም!” የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል፡፡ እውነት ነው የ‘‘ኢትዮጵያ”ን የሚያህል ብሄራዊ ቡድን ይዞ “አትናገሩኝ” ማለት አይችልም፤ ጫናን ካልፈለገ እና ከሸሸ ደግሞ ተመልሶ የአዳማ ህፃናትን ማሰልጠን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሆኖም ግን ሆነ ተብሎ ጉዳት ለማድረስ የሚደረግ ዘገባ (Harm Inflicting Reporting)፣ ኢ-ስፖርታዊ እና ኢ-ፍትሀዊ የሆኑ ግፊቶች (Unsportsmanlike and unfair pressures)፣ የግል ጥቅምን መሰረት ያደረጉ ግብ ግቦችን (Self-serving objectives) በግልፅ ለማየት ችያለሁ፡፡ ለዚህም ሆነ ተብለው የተቀረፁ አጀንዳዎች፣ ስራዬ ተብለው የተሰሩ ዘገባዎች እና ካምፔይኖችን አንድ በአንድ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ እግር ኳሳችንን በድርብ መነፅር ለሚከታተል ቤተሰብ እና ፓተርንን ለሚያነብ ባለሙያ ፍንትው ብሎ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሉባልታ እና ወሬ አውዳሚ መሳሪያዎች እንደሆኑ ስነቃላችን እራሱ ይናገራል «ጦር ከፈታው- ወሬ የፈታው» በሚል። እንደ አበው እና ስነቃሉ ከሆነ ጦርነትን ሸሽተህ ታመልጠዋለህ- ተሰደህ ታልፈዋለህ፤ ወሬን ግን ፍፁም ልትሸሸው አትችልም። በወሬ ምክንያት ብዙ ትዳሮች- ቤተሰቦች ፈርሰዋል፤ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች-ፖለቲከኞች ጥላሸት ተቀብተዋል፤ ንግዶች እና ነጋዴዎች ከስረዋል። ወሬ ምን ያህል አውዳሚ ስለመሆኑ ውበቱ ሌላው የእግር ኳስ ማስረጃ ነው።
አሁን ሀይላንድ እየተባለ በወል ስም የምንጠራው በሀገራችን ቀዳሚው የታሸገ የማዕድን ውሐ ከገበያ የወጣበት ምክንያት “ወሬ” እና “አሉባልታ” እንደሆነ ተደጋግሞ ተገልፆል፡፡ “ከሽንት ቤት ጋር የተቀላቀለ ውሀ ነው” በሚል በሚዲያ በተፈበረከ የጋዜጣ ወሬ ምክንያት ትልቅ ባለሀብት እና ትልቅ ፋብሪካ ከጨዋታ ወጥተው ቢዝነሱ ለሌሎች እንዲመቻች ተደርጓል፡፡ ውበቱንም ከዚህ «ፋብሪካ» ለይቼው ለማየት ያስቸግረኛል፤ ለአመታት ከአዳማ አቧራማ ሜዳዎች ጀምሮ ላቡን ያፈሰሰበት፤ ኳስ በወስፌ እየሰፋ ያደራጀው ህልም በዚህ መልኩ እንደተሰናከለበት አምናለሁ፡፡
እንደ ማህበረሰብ በወሬ እና አሉባልታ የሰዎችን ስራ ማጠልሸት፣ የፍላጎታቸው መሻት እንዳይደርስ ማድረግ፣ እንጀራ ማስጣልና መሰናክል መሆን በየቦታው የሚታይ ችግር ይመስለኛል፡፡ አጠቃሎ መፈረጅ ቢከብድም በማህበራዊ ሳይንስ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ማህበረሰብ የቃል ማህበረሰብ (Oral Society) በሚል የሚመደብ ሲሆን አብዛኛው እውቀት እና መረጃ በአፈ ታሪክ፣ በተረት፣ በንግግር እና በስነ ቃል ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ ቢኖረውም ሰው ካየው እና ከነካው ይልቅ የሰማውን እያመነ፣ ከተግባር እንቅስቃሴ ይልቅ ለወሬ የቅድሚያ ቅድሚያ እየሰጠ “አንደበተ ርዕቱዎቸ” እየገነኑ “ዝምተኞች” እየቆረቆዙ፣ “ወሬኞች” ፊት ፊት እያሉ የተግባር ሰዎች እየተገፉ የሚሄዱበት ሁኔታ በእጅጉ ተፈጥሯል፡፡ የሚፅፉ፣ የሚመራመሩ ሁሉ በሚያወሩ እና በሚናገሩ ሰዎች እየተሸፈኑ እና እየተሸነፉ የሚገኙት በዚህ አጠቃላይ ማህበራዊ ቅርፅ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
በቅርቡ በሀገራችን በተከሰተው የሰሜኑ ጦርነት ላይ ከመድፍ እና ከታንክ እኩል “ወሬ” ከፍተኛ የትግል ስልት እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ የሚሰሩብን ዘገባ ምን ያህል ውስጣችንን ይሰረስረው እንደነበር የትላንት ትውስታችን ነው። እንደእኔ ውበቱን ትጥቅ ያስፈታው እና የመልቀቂያ ወረቀት እንዲያቀርብ ያደረገው የጊኒው ሽንፈት ሳይሆን ይሄ “ወሬ” እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ወሬው በራሱ፣ በቤተሰቡ፣ በልጆቹ እና በአካባቢው ዙሪያ በሚገኙ ሰዎች የፈጠረውን ጫና በቅርበት አጫውቶኛል፡፡ ልጆቹ ትምህርት ቤት በሌሎች ልጆች እየተፌዘባቸው እና ሞራላቸው እየተነካ (ከአንድ ክለብ ብር ወስዷል በሚል ዘገባ ከተሰራበት በኋላ) በማስቸገሩ ስራውን ያስብበት እንደነበር ቀድሞውንም አውቅ ነበር፡፡
ይሄ ማለት ግን በውበቱ አባተ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች እና የቀረቡ ሙግቶች በሙሉ ተራ ስም ማጥፋት እና አሉባልታዎች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶች እርሱን አቅርበው፣ ሌሎች ደግሞ የዘገባ ሚዛናዊነቱን ጠብቀው ለእርሱም ሆነ ለኳሱ ይጠቅማል ያሉትን ሀሳብ ያለምንም የጀርባ አጀንዳ እና ግዝገዛ አቅርበዋል፡፡ የእነርሱን የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ትንታኔ ሰምተን፣ አስተያየታቸውን ወስደን ቡድናችንን የመረመርንበት ጊዜ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚም ለእነርሱ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

ይህንን ሁሉ ለመናገር የወደድኩት ለውበቱ ጥብቅና ለመቆም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ እየሄደበት ያለበት ሐዲድ ስለሚያሳስበኝ ነው፡፡ በእግር ኳሳችን ውስጥ “ስውር እጆች” እያቆጠቆጡ መተዋል፡፡ ክለብንም ሆነ ብሄራዊ ቡድንን ከኋላ ሆነው የሚነዱ ፡ “የኋላ ወንበር ሹፌሮች” (Back Seat Drivers)፣ በተጨዋቾች ዝውውር ተሰሚነት ኖሯቸው አላግባብ ጥቅም የሚያገኙ፣ አሰልጣኝ በማባረር እና በማስቀጠር ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው፣ ከአንዳንድ ደጋፊዎች ጋር ተሞዳሙደው ስቴዲየም ውስጥ የፈለጉትን የሚያስወድሱ፣ ያልፈለጉትን ደግሞ የሚያዘልፉ ስውር እጆች አሁን አሁን በርክተዋል፡፡ በሆቴል ኪራይ፣ በመኪና ኪራይ፣ በትጥቅ ግዢ፣ በውጭ ሀገር ጉዞ፣ በዶላር ምንዛሪ እና በመሳሰሉት ሁሉ እነርሱ ካልገቡበት የማይጥማቸው፣ ከውጤት ይልቅ የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ፥ ኢትዮጵያን እና እግር ኳስን ሽፋናቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ውበቱ ለእነዚህ የኋላ ወንበር ሹፌሮች አልተመቸም፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት ለመወያየት፣ ለመከራከር፣ ለመነጋገር ቦታ እንደሚሰጠው ሁሉ የውሳኔ መስመሩን ለማንም አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ለመጣ ለሄደው የማያጎነብሰው ውበቱ “የወታደር ልጅ እኮ ነኝ፤ እንዴት ይቻለኛል” ሲል ዘወትር አዳምጠው ነበር፡፡
እነዚህ ስውር እጆች የእርሱ ትከሻ ለትከሻ መለካካት የተመቻቸው አይመስልምና ያላቸውን በትር በተከታታይ ለአመታት አነሱበት- “ወሬ”፡፡ ቡድኑ ሲያሸንፍም ይወራል፣ ሲሸነፍም ይወራል፣ ሲኒየር ተጨዋቾችን ሲጠቀምም ይወራል፣ ሲያስቀምጣቸውም ይወራል፣ ስናሸንፍ «በእድል ነው»፣ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ «በኒጀር ነው»፣ ጥሩ ስንንቀሳቀስ «ተጋጣሚያችን ስለማይችል ነው»፣ ስናገባ «ጠልዘን ነው»፤ ከዚህ በተቃራኒው ስንሸነፍ «እከሌን ስላላስገባን ነው፤ አቋቋማችን ጥሩ ስላልሆነ ነው» አንድ ቀን እንኳን በእድል ተሸንፈን አናውቅም።
እነዚህ ውበቱን ጎዳን በሚል የተሰሩ ዘገባዎች ብሄራዊ ቡድኑ ላይ ጫናን፣ በቡድን አባላት መሀከል መከፋፈልን፣ መጠራጠርን ፈጥሮ እንደነበር እማኝ እሆናለሁ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ጥላሸት ሲቀባ፣ የቡድኑ አባላት ድካም እና ልፋት በከንቱ ውሀ ሲቸለስበት፣ የተጨዋቾች ላብ ሲቀለድበት ውበቱን አጠቃን ተብሎ ስራችን ሲታወክ መመልከት የዘወትር ህመማችን ነበር። በተለይም የጨዋውን የእግር ኳስ ቤተሰብ አመለካከት በመበረዝ የእርሱን እና የተለያዩ ተጨዋቾች ፎቶ በየሶሻል ሚዲያው ተዘቅዝቆ እንዲሰቀል፥ ምስላቸው በቀይ ቀለም የኤክስ ምልክት እየተደረገበት እንዲለጠፍ ተደርጓል። እኔም እንደአቅሚቲ «ተቀያሪ ወንበር ላይ የተቀመጡት ተጨዋቾች አዝነዋል፤ ውበቱ በትውውቅ ይዞት የሄደው ሳይኮሎጂስት ምን እየሰራ ነው» የሚለው የአንዱ የቴሌቪዥን ዘገባ እስከ አሁን ፈገግ ያሰኘኛል።
እንደ ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ በውበቱ ላይቤሪያ መሄድ የምትጎዳ እንጂ በየትኛውም መመዘኛ የምትጠቀም ሀገር ትሆናለች ብዬ አላስብም።የላይቤሪያ የእግር ኳስ ደረጃም ከፍ ያለ ባለመሆኑም በውበቱ ደረጃ ላለ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ የምመኘው አይነትም ስራ አይደለም። መሄዱም ቢሆን እንደ ስኬት እና ገድል ሳይሆን ለኢትዮጵያ እንደጉድለት ሊታይ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ዛሬ ውበቱም ተሰዷል-ብሄራዊ ቡድኑም ከእሽክርክሪቱ ወጥቷል። ያ ሁሉ ውርጅብኝ ይወርድበት የነበረው ብሄራዊ ቡድን አሁን የሚያወራለትም የሚያወራበትም የለም። በተከታታይ ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለቻን ማለፍ የቻለው ብሄራዊ ቡድን አሁን አሰልጣኝ እንኳን የለውም። የዛሬ 5አመት ውበቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት ኢትዮጵያ በፊፋ ደረጃ 147ኛ ላይ ተቀምጣ የነበረ ሲሆን በሂደት ግን ብሄራዊ ቡድኑ 9 ደረጃዎችን አሻሽሎ ወደ 138ኛ ዝቅ ለማለት ችሎ ነበር። አሁን ከውበቱ ስንብት ሶስት አመታት በኋላ ግን ይህ አሀዝ ሀያዎቹ ቤት መሆን ሲገባው ተመልሶ 147 ላይ ተገኝቷል- በዚህ ስሌት 20 ታሳቢ ደረጃዎችን ወደ ኋላ ተጉዘናል ።
ይብዛም ይነስም ያ በግንባታ ላይ የነበረ ብሄራዊ ቡድን ከውበቱ በኋላ በሶስት አሰልጣኞች ሰልጥኖ አሁን አራተኛውን እየናፈቀ በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ ይገኛል። ብሄራዊ ቡድን የቅብብሎሸ ስራ ነው እና በእርሱ እና በተከታዮቹ መሀከል የተደረገው ሽግግር ተፈጥሯዊ አለመሆኑን ተከትሎ ብሄራዊ ቡድኑም ሆነ የሙያ አጋሮቹ ሲቸገሩ አስተውያለሁ።
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ የማገለግላት ሀገር ናት፥ እንደ ዘርፍ ስፖርት እንጀራዬም ሙያዬም ነው። እግረ መንገዱን ወደ ስፖርቱ ለመጣ፥ ስፖርቱን መንገድ አድርጎ እና ተረማምዶበት ሊያልፍ ለሚፈልግ ሰው ወይም ቡድን የምመች ሰው መሆንን አልሻም። እንደዘመኑ «መሰገጥ» ባልፈልግም ጨዋ ጨዋ በመጫወት፣ አጉል ዲፕሎማት በመሆን፣ የነገ ጥቅሜን ከግምት በማስገባት የምናገር እና የምፅፍ ሰው አይደለሁም፤ እኔም ላይ ሊነሱብኝ ይችላሉ በሚል መሸበብም አልፈልግም፤ ከእነ ሙሉ ክብሩ፥ ጥቅሙ እና ግዴታዎቹ ያገኘሁት ዲግሪ ወይም ትምህርት እንዲህ እንድሆን አይፈቅድልኝም።
ስለፀሐፊው
ፀሐፊው ሳሙኤል ስለሺ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ት/ክፍል የእግር ኳስ እና የስፖርት ስነልቦና መምህር ሲሆኑ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። በአሁኑ ሰዓትም በጀርመን ስፖርት ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ስፖርት ልማት እና ፖለቲካ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ናቸው።


