የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች | የሦስተኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ

የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች | የሦስተኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ

ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚሻገር ቡድን የሚለይበት ኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ 70 እንደርታ የሚያፋልመው የሦስተኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ነገ 9፡30 ይደረጋል።

አዳማ ከተማን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ወደ ሦስተኛው ዙር የተሻገሩት እና በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች 3 ድሎች 2 አቻ እና 4 ሽንፈቶች አስመዝግበው በ 11 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቡናማዎቹ  ገጥሟቸው ከነበረው የውጤት መጥፋት አገግመው በጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ።

በሊጉ ከገጠማቸው 3 ተከታታይ ሽንፈት አንሰራርተው በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ድሎች እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ ቡናማዎች በቅርብ ሳምንታት ከውጤቶቹ ባሻገር በአወንታነቱ የሚጠቀስ መሻሻል አሳይተዋል። ባሻገርም ከ3ኛው እስከ 6ኛው ሳምንት ድረስ በተከናወኑ 4 መርሐ-ግብሮች ላይ በ3ቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ የወጣው የፊት መስመራቸው በመጨረሻዎቹ 3 ጨዋታዎች 3 ግቦችን በማስቆጠር ተስፋ ሰጪ መሻሻል አሳይቷል። በፊት መስመራቸው ላይ የታየው መነቃቃት ማስቀጠልም ከተጋጣሚያቸው የመከላከል ድክመት አንፃር በነገው ጨዋታ የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ተብሎ ይታመናል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአምስት ዓመታት ቆይታቸው ለመጀመርያ ጊዜ በሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በሲቢኢ ፕሪምየር ሊግ  አስከፊ አጀማመር በማድረግ ላይ ከሚገኙ ክለቦች ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው ዙር በአሸናፊ ሀፍቱ ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማን አሸንፈው ወደ እዚህ ዙር የተሻገሩት ምዓም አናብስት የወጥነት ችግር ቢስተዋልበትም በማጥቃቱ ረገድ በአወንታነት የሚጠቀስ ጥንካሬ አላቸው።  ያልተገባ ተጫዋች አሰልፈው ከተላለፈባቸው የነጥብ እና የግብ ቅነሳ በፊት በተካሄዱ 6 ጨዋታዎች ላይ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ከነበረው ሲዳማ ቡና እንዲሁም በጣምራ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ከነበሩት ሀዋሳ ከተማ እና መቻል ቀጥለው በወቅቱ 3ኛ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን መቻላቸውም የዚህ ማሳያ ነው። ሆኖም ደካማው የመከላከል አደረጃጀታቸው የቡድኑ ዋነኛ ችግር ነው። በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ካስተናገዱ ክለቦች አንዱ የሆነው ቡድኑ በቅጣት እና በጉዳት የተመናመነው የኋላ ክፍሉ ላይ የሚያደርገው ጥገናም ከጨዋታው ይዞት የሚወጣውን ነጥብ ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ ነው።

የነገው ጨዋታ ከመጨረሻዎቹ 3 ጨዋታዎች 7 ነጥብ የሰበሰበው ኢትዮጵያ ቡና እና በተጠቀሱት ጨዋታዎች 2 ነጥብ ያገኘውን መቐለ 70 እንደርታን እንደ ማገናኘቱ የአሸናፊነት ግምቱ ወደ ቡናማዎቹ የሚያዘነብል ቢሆንም ምዓም አናብስት በ3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሽንፈት ያልቀመሰውን ፋሲል ከነማ አሸንፈው ወደ እዚህ ዙር እንደ መብቃታቸው ቀላል ግምት እንዳይሰጣቸው ያደርጋል።