የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ የሸገር ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ሲዳማ ቡናዎች መሪነታቸውን ያሰፉበት ድል አስመዝግበዋል።
ሸገር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በአ.ሳ.ቴ.ስ የተካሄደ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ቁጥጥር የተደረገበት ሲሆን ሙከራ በማድረግ ረገድም ሸገር ከተማዎች ቀዳሚ ነበሩ። አንተነህ ተፈራ በ18ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ግጭቶ ያደረገው ሙከራም የጨዋታው የመጀመርያው ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።
በ20ኛው ደቂቃ ላይም ዘነበ ከድር ከሜዳው የግራ ክፍል ያሻማውን ኳስ በቅርቡ በተካሄደው የ17 ዓመት በታች የሴካፋ ዞን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ላይ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ወጣቱ ዳዊት ካሳው ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ሸገር ከተማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ለተቆጠረባቸው ግብ ምላሽ ለመስጠትም አስራ አንድ ደቂቃዎችን ብቻ ነበር የፈጀባቸው። በ31ኛው ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል። በአጋማሹ የመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር በባንኮች በኩል እንዲሁም ናትናኤል ዘለቀ በሸገር ከተማ በኩል የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉበት የጨዋታ ምዕራፍ ነበር።
72ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ተፈራ ከፍቅሩ አለማየሁ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂ ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ በሸገር ከተማ በኩል፤ 74ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳይመን ፒተር ከሳጥን ውስጥ መሬት ለመሬት መቷት ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ በንቃት ግብ ከመሆን ያዳናት ሙከራ ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ናቸው። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና
በሳምንቱ ተጠባቂ ከነበሩት ጨዋታዎች መሀል አንዱ በነበረው ጨዋታ ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ነበር ግብ የተስተናገደበት። መስፍን ታፈሰ 2ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ወደ ግብ መቷት የሀዲያ ተከላካዮች በአግባቡ ያላራቋትን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብም ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቡ መቆጠር በኋላም ሁለቱ ቡድኖች በፈጣን ሽግግሮች ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ከረጅም ርቀት አክርሮ ባደረገው እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሄኖክ አርፊጮ ከቅጣት ምት በሞከረው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።
የአጋማሹ መደበኛ ሰዓት እንዲሁም ተጨማሪ የባከኑ ደቂቃዎች ተጠናቅቀው የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ላይም ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ግብ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናዎች 2-0 እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለት ግቦች የተቆጠሩባቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች በቁጥር በዛ ብለው ግቦችን ማደን የጀመሩ ሲሆን በተቃራኒው ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገዋል። ጥቂት ሙከራዎች በተደረጉበት አጋማሽም ሲዳማ ቡናዎች ብርሃኑ በቀለ ባደረገው እንዲሁም ሀድያ ሆሳዕናዎች በፀጋአብ ግዛው አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግቦችን ሳንመለከት ጨዋታው በሲዳማ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ ሲዳማ ቡና በተከታታዩ ፋሲል ከነማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል።

