በ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ የአዲስ አበባ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ 0-0 ተለያይተዋል።
በዋና ዳኛ መለሠ ንጉሤ መሪነት በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር የተደረገበት ነበር። የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራም 28ኛው ደቂቃ ላይ በጣና ሞገዶቹ አማካኝነት ሲደረግ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ወንድወሰን በለጠ መትቶት በተከላካይ ሲመለስ ከሳጥን አጠገብ ሆኖ ያገኘው ግርማ ዲሳሳ በጥሩ ዕይታ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዐብዩ ካሣዬ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

በብርቱካናማዎቹ በኩል ቀደም ብሎ ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አድርጎ የነበረው አሥራት ቱንጆ 31ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ በድጋሚ ያደረገውን ጥሩ ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ይዞበታል።
ጨዋታው 39ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ባህር ዳሮች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሄኖክ ይበልጣል ዮሐንስ ደረጄ ወደኋላ በመመለስ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ድንቅ ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ በተለይም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደራጅቶ በመድረሱ በኩል ብልጫ በመውሰድ አጋማሹን የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ 56ኛው ደቂቃ ላይ ጎል የሚያስቆጥሩበት ወርቃማ ዕድል ፈጥረው ነበር። ሄኖክ ይበልጣል ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ወንድወሰን በለጠ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ከዚህ ሙከራ በኋላ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የደረሱት ብርቱካናማዎቹ 58ኛ ደቂቃ ላይ ያገኙትን የማዕዘን ምት ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሲያም ሱልጣን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አቤል ነጋሽ ነጻ ሆኖ ቢገጨውም ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በቀሪዎቹ ደቁቃዎችም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

