የዋልያዎቹ አለቃ ሆነው የተሾሙት አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳሕሌ ከዐፄዎቹ ጋር እንደሚለያዩ ይፋ ሆኗል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳሕሌ ከሹመታቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው ዕለት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ አድርገዋል። ከሁለት ሰዓታት በላቀው ቆይታ በርከት ያሉ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ጥያቄ የሆነው የፋሲል ከነማ ቆይታቸው ጉዳይን በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል።

በክረምቱ አሠልጣኝ ውበቱ አባተን ተክተው የዐፄዎቹ አለቃ ሆነው የነበሩት አሠልጣኙ በሊጉ ድንቅ አጀማመት በማድረግ እስካሁን ብቸኛ ያልተሸነፈ ቡድን በመገንባት በደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ ቦታ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በቶሎም በፋሲል ደጋፊዎች ልብ ውስጥ መግባት ችለው ነበር። ሆኖም ከቀናት በፊት ከመጣላቸው ሀገራዊ ስራ በኋላ ከቡድኑ ጋር በመቀጠል በጣምራ ይሰራሉ ወይስ ትኩረታቸውን በብሔራዊ ቡድን አርገው ይሰራሉ የሚለው ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።
ዛሬ በተሰማው መረጃ መሰረትም አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳሕሌ ከፋሲል ከነማ ጋር ያላቸውን ውል አቋርጠው በብሔራዊ ቡድኑ ስራ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።
በ14ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ተጠባቂ በሆነው የሊጉ ፍልሚያ የፊታችን ቅዳሜ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚያደርገው ጨዋታም ዐፄዎቹን በይፋ እንደሚሰናበቱ ይጠበቃል።

