ክስተቱ ነገሌ አርሲ በካቤ ብዙነህ ብቸኛ ግብ ግስጋሴውን ሲያስቀጥል የወልዋሎ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ አንድ ለአንድ ተጠናቋል።

ሽረ ምድረገነት ከ ነገሌ አርሲ
7፡00 ሰዓት የጀመረው የሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የታየበት ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ ግን ነገሌ አርሲዎች ሙሉ ብልጫ የወሰዱበት ነበር።
ሰገኖቹ ከቤ ብዙነህ ከሳጥን ውጭ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ በኋላም በ12ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ካቤ ብዙነህ በረዥሙ ተሻግራ ዳዊት ተፈራ በጥሩ መንገድ ተቆጣጥሮ የሰነጠቃትን ኳስ ተጠቅሞ በግሩም አፈፃፀም ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ሰጎኖችቹን መሪ ማድረግ የቻለች ግብ ነች። ከግቡ መቆጠር በኋላም ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ነገሌ አርሲዎች ሮሆቦት ሶላሎ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ሪችሞንድ አይ በመለሳት እንዲሁም ካቤ ብዙነህ ከግራ መስመር አሻምቷት ምስጋናው መላኩ በግንባሩ ገጭቶ አግዳሚው በመለሰበት ወርቃማ አጋጣሚ መሪነታቸውን ለማጠናከር ተቃርበው ነበር። ሽረ ምድረገነቶች ግን በአጋማሹ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት እንዲሁም በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር።
በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው በተጫወቱት ሽረዎች በኩልም አቤል ማሙሽ ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
አጥቂው የመስመር ተጫዋቹ ክፍሎም ገብረህይወት በረዥሙ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ እንዲሁም
ስንታየሁ ዋለጬ አሾልኮለት ግብ ጠባቂውን ለማለፍ በሚያደርገው ጥረት እድሪሱ አብዱላሂ የተቆጣጠራት ኳስ ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ካቤ ብዙነህ ተቀይሮ ከገባው ዘሩባቤል ፈለቀ የተቀበለትን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው የመለሳት ድንቅ ሙከራ እንዲሁም በድጋሜ ካቤ ብዙነህ በሳጥኑ ግራ ክፍል ሁለት ተጫዋቾችን ካለፈ በኋላ ግብ ጠባቂው ሬችሞንድ አይ የተቆጣጠራት ኳስም የነገሌ አርሲ መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታም ሰጎኖቹ በካቤ ብዙነህ ብቸኛ ግብ ድል አድርገዋል። ተከታታይ አራት ድሎች ያስመዘገበው ቡድኑ ነጥቡን 25 በማድረስ ደረጃውን አሻሽሏል።
አዳማ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
በአዲስ አበባ ስቴድየም የተካሄደ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት እንዲሁም በተደጋጋሚ ጥፋቶች የታጀበ ነበር።
በአጋማሹ በአንፃራዊነት የተሻለ የፊት መስመር እንቅስቃሴ የነበራቸውና ስምዖን ማሩ ከመስመር አሻግሯት ሳጥን ውስጥ የነበረው ኮንኮኒ ሀፍዝ ባልተጠቀመባት አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት ቢጫዎቹም በ21ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ወንድሙ ባስቆጠራት ድንቅ የቅጣት ምት ግብ መሪ መሆን ችለዋል። በድምሩ 21 ጥፋቶች የተፈፀሙበትና ቀዝቃዛ የፊት መስመር እንቅስቃሴ በተስተዋለበት አጋማሽም አዳማ ከተማዎች ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
በሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች በአመዛኙ ወደ መከላከል ባዘነበለ አቀራረብ በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ስያደርጉ አዳማ ከተማዎች ደግሞ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የአቻነት ግብ ፍለጋ ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ብዙአየሁ ሰይፈ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት ለጥቂት በወጣችው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበሩት አዳማ ከተማዎችም በ74ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ቢንያም አይተን የዕለቱ ዋና ዳኛ ሄኖክ አክሊሉ ሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቷት በሚል የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት በመቀየር ነበር ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለው።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ወልዋሎዎች ኪሩቤል ወንድሙ ባደረጋት እንዲሁም ፍቃዱ መኮንን በረዥሙ ተሻግራ ኮንኮኒ ሀፍዝ በግንባሩ የጨረፋትን ኳስ አግኝቶ ከግቡ አፋፍ ሆኖ ባመከናት አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

