በ14ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን በአዲስ አበባ የተደረገው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

በዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግም በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ግን ኤሌክትሪኮች ብልጫ ነበራቸው።
በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ሲደርሱ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል እየተደራጁ ቢደርሱም ያለቀላቸውን የግብ ዕድሎች በመፍጠሩ በኩል ግን ክፍተት ነበረባቸው።
የጨዋታው የተሻለ ሙከራ 36ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የኤሌክትሪኩ ኢዮብ ገብረማርያም ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጪ በረጅሙ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣበት ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ አቤል ሀብታሙ ከቅጣት ምት በተሻገረ ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ብርቱካናማዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ሲቀሩ በርካታ አጋጣሚዎችን ያገኙት ኤሌክትሪኮችም አስቆጪ በሆነ አፈጻጸም ጎል ሳያስቆጥሩ ቀርተው ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ቀጥሎ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የድሬዳዋው መስዑድ መሐመድ እና የኤሌክትሮኒኩ ሀሰን ሁሴን ፈታኝ ያልሆኑ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 53ኛ ደቂቃ ላይ ፈጥረው አቤል ነጋሽ በጥሩ ሁኔታ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ለአሥራት ቱንጆ ወደ ውስጥ ቀንሶለት ሳይጠቀሙበት የቀሩት ኳስ አስቆጪ ነበር።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 67ኛ ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ያሬድ የማነ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያደረውን ሙከራ ግቡ ጠባቂው ዐብዩ ካሳየ ካገደበት በኋላ ወደ ግቡ አቅጣጫ የሄደውን ኳስ ተከላካዩ አሕመድ ረሺድ በግሩም ፍጥነት ከመስመር መልሶታል።
ይበልጥ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ድሬዎች 84ኛው ደቂቃ ላይ በአብዲሳ ጀማል እና በመሐመድኑር ናስር አማካኝነት ያደረጓቸውን ሙከራዎች ተከላካዮች ተደርበው ከመለሷቸው በኋላ ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች ሳይደረጉ ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።

