15ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ መርሐግብሮች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ወልዋሎ
በ16 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ እያደረጉት ባለው ጉዞ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ዛሬ ያከናውናሉ። መድኖች በመጨረሻው መርሐ ግብር ወላይታ ድቻን በማሸነፍ ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል። ከመመራት ተነስቶ ድል ባደረገበት ጨዋታ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው ቡድኑ በዛሬው ዕለት በተለይም በብዙ ረገድ የተሻሻለ እንቅስቃሴ አድርጎ ከስምንት መርሐ ግብሮች በኋላ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻለውን የፊት መስመሩ ጥንካሬ ማስቀጠል ይኖርበታል።
በ 11 ነጥቦች 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማሉ። ሁለት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገቡ በኋላ ባደረጓቸው አምስት መርሐ ግብሮች አራት አቻ እንዲሁም አንድ ሽንፈት ያስተናገዱት ወልዋሎዎች በቅርስ ሳምንታት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችሉም በፊት መስመር ላይ ባላቸው ደካማ አፈፃፀም እና በኋላ መስመሩ ላይ በሚስተዋለው የትኩረት ማነስ ድል ማድረግ አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ አራት መርሐ ግብሮች የጨዋታ መልክ የቀየሩ አንድ ቀይ ካርድ እና ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች ያስተናገዱው ቢጫዎቹ በዛሬው ጨዋታ መሰል ስህተቶችን ማረም ግድ ይላቸዋል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል አማኑኤል ኤርቦ፣ ዋንጫ ቱት፣ አብዱ ሞሐመድ፣ ታዬ ጋሻው እና ሚሸል ኦቶ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ለረጅም ወራቶች ጉዳት ላይ የቆየው ግብጠባቂው አቡበከር ኑራም ወደ ልምምድ ቢመለስም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በወልዋሎ በኩል ደግሞ ሙሉዓለም መስፍን ከጉዳት አገግሞ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ቢሆንም በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ ተቀይሮ የወጣው ሰመረ ሀፍታይ ግን ከጨዋታው ውጭ ነው።
ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን
ኢትዮጵያ መድን አንድ ጊዜ አሸንፎ አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ መድን 2 ግቦች ወልዋሎ ደግሞ 1 ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
ባህርዳር ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ
በ19 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች በሰንጠረዡ አካፋይ ባለው የነጥብ መቀራረብ ምክንያት የደረጃ መሻሻል ሊያስገኝላቸው የሚችል ድል ፍለጋ ምዓም አናብስትን ይገጥማሉ። በ14ኛው ሳምንት መቻልን በማሸነፍ ከናፈቃቸው ድል ጋር የታረቁት የጣና ሞገዶቹ በዕለቱ ያሳዩትን እንቅስቃሴ ማስቀጠል ቀዳሚ ተግባራቸው ይመስላል። በተለይም አራት በግብ ድርቅ የተመቱ የጨዋታ ሳምንታት ካሳለፈ በኋላ በጨዋታው በርከት ያሉ ዕድሎች በመፍጠር ሁለት ግቦች ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወት ጥንካሬ ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።
በ12 ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በቅርብ ሳምንታት ያሳዩትን መሻሻል በድሎች ለማጀብ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ድሎች እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገብ የቻሉት ምዓም አናብስት በተጠቀሱት መርሐ-ግብሮች ሽንፈት አልባ ጉዞ ማድረጋቸው እንደ አወንታ የሚጠቀስላቸው ነጥብ ቢሆንም በዛሬው ጨዋታ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ዕድሎችን የመጠቀም ድክመታቸውን መቅረፍ ይኖርባቸዋል።
በባህርዳር ከተማ በኩል ጉዳት ላይ ከሰነበተው አማኑኤል ገብረሚካኤል በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት ለጨዋታ ዝግጁ ሆኖ በመጨረሻ ሰዓት ጉዳት ያገረሸበት መሳይ አገኘሁ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው። መቐለ 70 እንደርታዎች በዛሬው ጨዋታ ጉዳት ላይ የሰነበቱትን ሱሌይማን ሐሚድ፣ ቦና ዓሊ፣ ዘርኢሰናይ ብርሀነ፣ አማኑኤል ልዑል እና ዮሐንስ ዓፈራ ግልጋሎት አያገኙም።
ሁለቱ ቡድኖች ከተሰረዙት ሁለት የ2012 የውድድር ዓመት ጨዋታዎች ውጭ በፕሪምየር ሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተዋል። የጣና ሞገዶቹ 2 ጊዜ ድል ሲያደርጉ ምዓም አናብስት አንድ ጨዋታ አሸንፈው በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎች ባህርዳር ከተማ 6 መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ 3 ግቦችን አስቆጥረዋል።

