የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ለማስተናገድ ዝግጅቱን መጨረሱ ተነግሯል።

ለሀገራችን የእግር ኳስ ዕድገት ዋነኛ እንቅፋቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ አለመኖር ሲሆን ይህንንም ችግር ለመቅረፍ እና ስደተኛው ብሔራዊ ቡድናችንን በሀገሩ ውድድር እንዲያደርግ በFIFA የወጣውን መስፈርት አሟልቶ ግንባታውን እያደረገ የሚገኘው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታዎቹ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሲሆን የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ2ኛ ዙር ጀምሮ ውድድሮችን ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቆ መጨረሱ ተገልጿል።
የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ጎሹ እንዳላማው ለክልሉ መገናኛ ብዙኀን እንደገለፁት “አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ሀገራችን ላይ ካሉ የውድድር ሜዳዎች ምቹ እና ተመራጭ የሆነ ሜዳ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች በከተማችን ይገኛሉ። ውድድሩ እዚህ መካሄዱ የተዳከመውን የባህር ዳር ዳር ኢኮኖሚ ዳግም እንዲያንሰራራ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው። ውድድሩ ወደ ባህር ዳር እንዲመለስ ጥያቄዎችን አቅርበን መልስ እየጠበቅን ነው።” ሲሉ ሀሳቸውን ሰጥተዋል።
የውድድሩ የበላይ አካል በቀጣይ የሚሰጠውን ምላሽ አካተን የምንመለስ ይሆናል።

