በአዳማ በተደረጉ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ በካርሎስ ዳምጠው ግቦች ድሬዳዋን 2-0 ሲያሸንፍ መቻል እና ምዓም አናብስት 0-0 ተለያይተዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው አሥራት ቱንጆ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ለመሐመድኑር ናስር ለማቀበል የሞከረውን ኳስ መልካሙ ቦጋለ በጥሩ ቦታ አያያዝ አግዶባቸዋል።
18ኛው ደቂቃ ላይ የጦና ንቦቹ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው መሳይ ሰለሞን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ፍሬው ጌታሁን አስወጥቶበታል።
በድሬ በኩል 34ኛው ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል በድቻ በኩል 42ኛው ደቂቃ ላይ ኪዳኔ አሰፋ ካደረጓቸው ሙከራዎች በኋላ ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርቀት ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ድሬዳዋ 49ኛው ደቂቃ ላይ በቁጥር ለማነስ ተገዷል። ድልአዲስ ገብሬ የድቻው መሳይ ኒኮል ላይ በሠራው አደገኛ ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷልለ
65ኛ ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። ካርሎስ ዳምጠው ኳስ እየገፋ በመውሰድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በድንቅ ሁኔታ መረቡ ላይ አርፏል።
የጦና ንቦቹ 79ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩበት አጋጣሚ አግኝተው ኪዳኔ አሰፋ በግሩም ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ያሬድ ዳርዛ በደካማ ሙከራ ኳሱን ለግብ ጠባቂው ፍሬው በቀላሉ አሳቅፎታል።
ካርሎስ ዳምጠው የቀድሞ ክለቡ ላይ 83ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ግዙፈ አጥቂ በዮናታን ኤልያስ ተመትቶ በአሕመድ ረሺድ የተመለሰውን ኳስ አግኝቶ ነው ግብ ያደረገው።
ወላይታ ድቻ 87ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛ ግብ ሊያስቆጥር የሚችልበት እጅግ ወርቃማ ዕድል አግንኝቶ ዮናታን ኤልያስ ከግራ መስመር ባሻገረው ኳስ ከክፍት መረብ ጋር የተገናኘው ቸርነት ኡፋይሳ ለማመን በሚከብድ መልኩ ዕድሉን አምክኖታል።
መቻል ከ መቐለ 70 እንደርታ
ቦና ዓሊ 22ኛው ደቂቃ ላይ አክርሮ መተቶት አልዌንዚ ናፊያን በያዘበት ሙከራ የግብ ዕድሎችን በማስመልከት በጀመረው የአመሻሹ ጨዋታ መቻሎች 43ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ዓለምብርሃን ይግዛው ከፍ አድርጎ ባቀበለው ኳስ ቻርለስ ሙሴጌ በደረቱ አብርዶ በመምታት ያደረገውን አስደናቂ ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ ሲመልስበት ያንኑ የተመለሰ ኳስ ያገኘው ዮዳሄ ዳዊት የመታው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ አጋማሹን የጀመሩት መቻሎች 55ኛ ደቂቃ ላይ በብሩክ ማርቆስ አማካኝነት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ዓለምብርሃን ይግዛው ያሻገረውን ኳስ ቻርለስ ሙሴጌ በግንባሩ ሳይገጨው በመቅረቱ የግብ ዕድሉን ሲያባክነው 65ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በድንቅ ሁኔታ ተጫዋቾችን እያለፈ ይዞት በገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።
እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታም ተጨማሪ ተጠቃሽ የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

