ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ22ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ22ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

22ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት መርሐግብሮች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ነጌሌ አርሲ

ሀያ አራት ነጥቦች ሰብስበው 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመራቅ የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። ድሬዳዋ ከተማን አራት ለባዶ ካሸነፉበት የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ድል ማድረግ ያልቻሉት ፈረሰኞቹ በመጨረሻዎቹ 12 መርሐ ግብሮች ውስጥ ማሸነፍ የቻሉት በአንዱ ብቻ ነው፤ ይህንን ተከትሎም ከደረጃ ከሰንጠረዡ ወገብ አሽቆልቁለው ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ ርቀት ብቻ ለመቀመጥ ተገደዋል። ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ፈተና ውስጥ የገባው ቡድኑ ከዚህ አስከፊ የውጤት ማሽቆልቆል ለማገገም በመጨረሻዎች አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ እና በተጠቀሱት መርሐ ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመሩን ማሻሻል ይጠበቅበታል።

በሰላሣ ስድስት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነጌሌ አርሲዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው በመጨረሻው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት ሰጎኖቹ ድል አድርገው መሪዎቹን እግር በእግር መከታተልን እያለሙ በሚያከናውኑት የዛሬው ጨዋታ በሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በሁለተኛው ዙር በተከናወኑ መርሐ ግብሮች በቀደመ ውጤታማነቱ መዝለቅ ያልቻለውን የማጥቃት ክፍላቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተገኑ ተሾመ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆን የአዲሱ አቱላ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ነጌሌ አርሲዎች በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው አብዱልባሲጥ ከማል በተጨማሪ አማካዩ ዳዊት ተፈራ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም። በቅጣት በመጨረሻው ጨዋታ ያልተሳተፈው ርሆቦት ሶላሎ ግን ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአቤል ያለው ብቸኛ ግብ ማሸነፉ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ መቻል

24 ነጥቦችን ሰብስበው 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመራቅ ወሳኝ ድል ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል። ፋሲል ከነማ ላይ ባስመዘገቡት ወሳኝ ድል ሁለተኛውን ዙር ጀምረው በመጨረሻው ጨዋታ በሽረ ምድረ ገነት ሽንፈት ያስተናገዱት ሀምራዊ ለባሾቹ በሊጉ ከዛሬው ተጋጣሚያቸው መቻል ጋር በጣምራ ከፍተኛ የግብ መጠን በማስመዝገብ ቀዳሚ ቢሆኑም በአንፃሩ 27 ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ ቀዳሚ ነው። ይህንን ተከትሎም የመከላከል አደረጃጀቱን ማሻሻል የቡድኑ ቀዳሚ ስራ መሆን ይኖርበታል።

በሰላሣ አንድ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ከፍ የሚያደርጋቸውን ድል ለማግኘት ይፋለማሉ።
መቻሎች ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ካስገኙላቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም። ሁለት ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤት አስመዝግቦ ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን ጥሎ ሁለቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ የተሻለ ጫና በፈጠረበት የመጨረሻው ጨዋታ ነጥብ መጋራት ቢችልም እንዳለው ጥራት በወጥነት መዝለቅ ያልቻለውን የማጥቃት ክፍሉን ማሻሻል እንዲሁም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍሉ ድክመት መቅረፍ ግድ ይለዋል።

በንግድ ባንክ በኩል አዲስ ግደይ ፣ ካሌብ አማንክዋህ እና ዮናስ ለገሰ ልምምድ መጀመራቸው ቢሰማም ለዛሬው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር በአሰልጣኙ የሚወሰን ይሆናል።

በመቻል ውብሸት ጭላሎ እና ዮሐንስ መንግስቱ ዛሬም ግልጋሎት የማይሰጡት ሲሆን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በቅጣት ያልነበረው ግሩም ሐጎስ ከቅጣት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ30 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቻል 11 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ባንክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 14 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 41 ሲያስቆጥር ባንክ 32 አስቆጥሯል።

ሸገር ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

ከዛሬ ተጋጣሚያቸው እኩል 23 ነጥብ ሰብስበው በግብ ክፍያ ተበልጠው 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገር ከተማዎች የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ በተካሄደው እና ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ሸገር ከተማዎች ዛሬ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት ይፋለማሉ። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ በሊጉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ ከሆነው ባህርዳር ከተማ በመቀጠል ከሌሎች ሁለት ክለቦች ጋር በጣምራ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከዚህ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ አባዜ ለመላቀቅም በአራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻው መርሐ ግብር ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው የፊት መስመሩን ውጤታማነት ማስቀጠል ይኖርበታል።

23 ነጥቦች ሰብስበው 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ጋር ይፋለማሉ።
በ14ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን ሁለት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ በስድስት ጨዋታዎች ድል ሳያደርጉ ዘልቀው በመጨረሻው መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ የቻሉት መድኖች በጨዋታው የነበሯቸውን አወንታዊ ጎኖች ማስቀጠል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል። በተለይም ሁለት ሽንፈቶች እና አራት የአቻ ውጤቶች ባስመዘገቡባቸው ስድስት መርሐ ግብሮች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ዘልቆ በመጨረሻው ጨዋታ ሦስት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመሩ በጨዋታው የነበረውን ውጤታማነት ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

በሸገር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ከቅጣት እና ጉዳት ነፃ ሁነው የዛሬው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በኢትዮጵያ መድን በኩል ዋንጫ ቱት እና ረመዳን ሁሴን አይኖሩም።

ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች በአማኑኤል ኤርቦ ብቸኛ ግብ ድል ማድረጋቸው ይታወሳል።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ሽረ ምድረ ገነት

በሀያ አንድ ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚደረገው ፍልሚያ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያደርጋሉ። በመጨረሻው መርሐ ግብር ከመመራት ተነስተ ፋሲል ከነማን ሁለት ለአንድ ማሸነፍ የቻለው ቡድኑ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ያገኘውን እጅግ ወሳኝ ድል ለማስቀጠል በቅርብ ሳምንታት ያሳያቸውን አወንታዊ መሻሻሎች ማጠናከር ይጠበቅበታል። የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡናና 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን ፋሲል ከነማ በገጠሙባቸው ፈታኝ መርሐ ግብሮች አራት ነጥብ ያሳኩት ቢጫዎቹ ከውጤቱ ባሻገር ያሳዩት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነበር። በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ተስፋቸው ለማለምለምም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ያሳዩትን እንቅስቃሴ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

ሀያ ስድስት ነጥብ ሰብስበው 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረገነቶች ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ የሚሉበትን ድል ለማግኘት ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እየታገለ የሚገኘውን ወልዋሎ ይገጥማሉ።

ደሳለኝ ከተማ በጨዋታው መገባደጃ ባስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሁለት ለአንድ አሸንፈው
ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ሽረ ምድረገነቶች በሰንጠረዡ አካፋይ ባለው የነጥብ መቀራረብ መነሻነት ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚችሉበትን ዕድል ለማመቻቸት የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆኑ መርሐ ግብሩ ወሳኝ ነው።  አርባ ምንጭ ከተማን ካሸነፉበት የ16ኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሦስት የአቻ ውጤቶችና አንድ ሽንፈት አስመዝግበው  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በገጠሙበት መርሐ ግብር ከድል ጋር የታረቁት ሽረዎች በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ለማግኘት በአራት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ዘልቆ በመጨረሻው መርሐ ግብር የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወት ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

ወልዋሎዎች በጉዳት ምክንያት የያሬድ ከበደን ግልጋሎት አያገኙም።  በሽረ ምድረ ገነት በኩል አንተነህ ተስፋዬ እና ተካልኝ ደጀኔ ከቅጣት ሲመለሱ አቤል እንዳለ እና ጎይትኦም ነጋ ግን በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው ስሑል ሽረ 2 ጊዜ ድል ማድረግ የቻለ ሲሆን ወልዋሎ 1 አሸንፏል በቀሪው 2 ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። በአጠቃላይ 7 ጎሎች ሲቆጠሩ ስሑል ሽረ 4 ወልዋሎ ደግሞ 3 ግብ አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው 2012 ጨዋታ አልተካተተም)።