በሙከራዎች የታጀበ አዝናኝ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ ምዓም አናብስትን 2ለ1 ረተዋል።

ምዓም አናብስት እና ብርቱካናማዎቹ ያገናኘው በዕለቱ በአዳማ የተካሄደ ብቸኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ አዝናኝ በሙከራዎች የታጀበና ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን ግብ የተቆጠረውን ገና በጅማሮው ላይ ነበር። ሦስተኛው ደቂቃ ላይ ዓብዱሰላፍ የሱፍ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ያስቆጠራት ግብም ድሬዳዋ ከተማን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ምዓም አናብስት ስንታየሁ መንግስቱ ከግራ መስመር ተሻምታ አሸናፊ ሀፍቱ ያመቻቻትን ኳስ አግኝቶ ባልተጠቀመባት ወርቃማ ዕድል እንዲሁም ቦና ዓሊ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት አብዩ ካሳየ ባዳናት ሙከራ እና ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። መሪነቱን ከጨበጡ በኋላ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ብርቱካናማዎቹም አብዲሳ ጀማል ከሳጥን ውጭ ከፍ አድርጎ ካደረጋት ሙከራ በኋላ አቤል ነጋሽ ከአቡበከር ሻሚል የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ቋሚውን በመለሰበት አጋጣሚ መሪነታቸውን ለመስፋት ተቃርበው ነበር።

በአጋማሹ በማጥቃቱም ይሁን ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ብልጫ የነበራቸው መቐለዎች በፍፁም ዓለሙ አማካኝነትም ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን አማካዩ ከአሸናፊ ሀፍቱ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ዓብዩ ካሳየ ወደ ውጭ ያወጣት እና ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስም ምዓም አናብስትን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። ከተጠቀሱት አጋጣሚዎች በተጨማሪም ቦና ዓሊ እንዲሁም
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቆመ ኳስ ሞክሮት አብዩ ካሳዬ ያዳነው ሙከራም ይጠቀሳሉ።
በድሬዳዋ ከተማዎች በኩልም አቤል ነጋሽ ከመስዑድ መሐመድ የተቀበላትን ኳስ አግኝቶ መቷት ግብ ጠባቂው በመለሳት እንዲሁም መስዑድ መሐመድ ‘በራቦና’ ሞክሯት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ባዳናት አጋጣሚ እና ጀሚል ያዕቆብ ከመስመር አሻምቷት አብዲሳ ጀማል በጥሩ መንገድ መቷት ግብ ጠባቂው እንደምንም ወደ ውጭ ባወጣት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ባይሆንም ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ግብ ያስተናገደው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ነበር፤ በ49′ ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ ከቆመ ኳስ አሻምቷት ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ከገጫት በኋላ ተመስገን ተስፋዬ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም መቐለ 70 እንደርታዎችን አቻ ማድረግ ችላለች። ሆኖም ድሬዳዋ ከተማዎች ዳግም መሪ ለመሆን የፈጀባቸው ሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር፤ አብዲሳ ጀማል በረዥሙ ተሻግራ አቤል አሰበ ያመቻቻትን ኳስ አግኝቶ ያስቆጠራት ግብም ብርቱካናማዎቹን ዳግም ወደ መሪነት መልሳለች።
የአቻነት ግቧን ማስጠበቅ ያልቻሉት ምዓም አናብስትም ስንታየሁ መንግስቱ ከመዓዝን የተሻማውን ኳስ አግኝቶ ባደረጋት ሙከራ እንዲሁም ቦና ዓሊ በራሱ ጥራት ያገኛትን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መቷት በዕለቱ ከ10 በላይ ኳሶች በማዳን ኮከብ ሆኖ ባመሸው አብዩ ካሳዬ በተመለሰች ኳስ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ብርቱ ፉክክር የታየበት እንዲሁም በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ጨዋታም በድሬዳዋ ከተማ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

