ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ሲያገኝ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

 

አዳማ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

ተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት አዳማዎች በ33 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የሊጉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የነበረው ቡድኑ አሁን ግን ያ ጥንካሬው እየራቀው ይገኛል። በሁለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ቀድመው ግብ ማስቆጠር ችለው የነበር ቢሆንም ውጤት ማስጠበቅ ባለመቻላቸው 4 ነጥቦችን ጥለዋል። ዛሬ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ስድስት የሚያጠብቡት አዳማዎች ተጋጣሚያቸው ባለፈው ሳምንት ከባድ ሽንፈት አስተናግዶ የመጣው እና ዛሬ የጥንቃቄ አጨዋወት እንደሚመርጥ የሚጠበቀው አርባምንጭ ከተማ እንደመሆኑ ለዛሬው ጨዋታ በተለይም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ቅንጅታቸውን ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት እየተጓዘ በነበረበት ሰዓት ባልተጠበቀ አጋጣሚ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 4ለ1 የተረመረመው አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በሁሉም ግብ ማስቆጠር መቻሉ ትልቁ ጥንካሬው ነው። ከወራጅ ቀጠናው ጫፍ ላይ ከሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በ9 ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ድል መቀዳጀት በሊጉ የመቆየት ተስፋውን በእጅግ የሚያለመልምለት ይሆናል። ሆኖም የባለፈውን ሳምንት ያልተጠበቀ ከባድ ሽንፈት የረሳ እና በዛሬው ጨዋታ በስነልቦና ረገድ ከፍ ያለ ዝግጅት ያደረገ ቡድን ሆኖ መቅረብ ይጠበቅበታል።

 

ቡድኖቹ በሊጉ 19 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 8 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ 5 አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አርባምንጭ 17 አዳማ 12 ግቦችን አስቆጥረዋል።

 

ሀዋሳ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

 

ከመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያገኙት ሐይቆቹ በተለይም ከእነዚህ ጨዋታዎች በፊት ከተደረጉ 7 ጨዋታዎች አንድ  ግብ ብቻ ተቆጥሮበት የነበረው የመከላከል አደረጃጀት በነዚህ ሦስት ጨዋታዎች አራት ግብ ማስተናገዱ ትኩረትን የሚሻው ጉዳይ ነው። የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ዛሬ ካሸነፉ ልዩነታቸውን ወደ ሁለት ማጥበብ የሚችሉት ሀዋሳዎች የዛሬ ተጋጣሚያቸው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት አልሞ ወደ ሜዳ የሚገባ ቡድን እንደመሆኑ ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ይገመታል።

ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ምዓም አናብስት ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ባለፉት 6 ሳምንታት አንድ ጊዜ ብቻ ያሳኩትን ድል መደጋገም ይኖርባቸዋል። ከአርባምንጭ ከተማ (14) ቀጥሎ ከባሕር ዳር ከተማ እኩል 15 ግቦችን ብቻ በማስቆጠር በሊጉ ዝቅተኛውን ግብ ያስቆጠሩት መቐለዎች በውጤት ባይታጀብም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ጠንካራ ወደነበረው የሊጉ መጀመሪያ ላይ የነበረውን የማጥቃት ውጤታማነት መልሰው ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች በቅጣት ምክንያት የአማካዩ አብነት ደምሴ ግልጋሎት አያገኙም። መቐለ 70 እንደርታዎች በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ቡድኖቹ  ከተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ውጭ በሊጉ 7 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ሦስት መቐለ ደግሞ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ፤ ሁለት ጨዋታ ደሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። ሀዋሳ 8 ( የመጀመሪያው ዙር የፎርፌ 3 ግቦች ጨምሮ ) ሲያስቆጥር መቐለ 4 ግብ አስቆጥሯል።