የኢትዮጵያ እግር ኳስ የከፍታ ማማ የነበሩት ፈረሰኞቹ አሁን ላይ በፅኑ ታመዋል ፤ አይነኬ የነበረው ቡድን በዚህ ልክ ከተዳከመ ታድያ ሌሎችስ ተስፋቸው እስከምን ድረስ ?!
አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በወርቅ ከታተመ የዘጠና ዓመታት የስኬት ታሪክ ጋር ዘንድሮ 90ኛ ዓመቱን ደፍኗል ፤ ታድያ እንዳለመታደል ሆኖ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ቡድኑ በዘመናዊ ታሪኩ ገጥሞት የማያውቀው አስተዳደራዊ እና ፋይናንሻል ውጥንቅጥ ውስጥ ይገኛል። እርግጥ የፈረሰኞቹ አሁናዊ ሁኔታ የዛሬ ብቻ ጉዳይ ሳይሆን ከትናንት የተንከባለሉ ችግሮች ድምር ውጤት እንደሆነ ቢታመንም አሁናዊ የክለቡ ሁኔታ ግን ከመቼውም ጊዜ የባሰ እንደሆነ እየተመለከትን እንገኛለን።
በአንድ ወቅት የሊጉ ከፍተኛ ከፋይ ፣ የከዋክብት ቀዳሚ መዳረሻ ፣ ከደሞዝ ባለፈ በጥቅማጥቅሞች የማይታማው ቡድኑ አሁን ላይ ደሞዝ በወቅቱ መክፈል እንደ ቅንጦት የሚታይበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ፤ ለወትሮው በውጤት ተሸፍኖ የነበረው አስተዳደራዊ ጉዳዮች አሁን ላይ አደባባይ ከተሰጡ ሰንብተዋል። ዘንድሮ በኢትዮጵያ ዋንጫ ከሁለተኛ ዙር መሻገር ያልቻለው ቡድኑ አሁን ላይ በሊጉ ደግሞ በ25 ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህም ሊጉ በአዲስ መዋቅር መካሄድ ከጀመረበት 1990 ጀምሮ ያልታየ ቁልቁለት ነው።
ከሁሉም ወደ ምንም
ትናንት ከቀትር በኋላ አዲሱ የዋልያዎቹ አለቃ ዮሀንስ ሳህሌ በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ ጋር ላለባቸው የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠቁማባቸውን የ23 ተጫዋቾችን ዝርዝር ይፋ ሲያደርጉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም ተጫዋቾች ያልተመረጠበት ምርጫ መሆኑ ክስተቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ምናልባትም ያልታየ መሆኑ ብዙዎችን ያስገረመ አጋጣሚ ነበር።
ይህ አጋጣሚ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁናዊ ቁመና ሌላ አይነተኛ ማሳያ ነው። ለዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክዋክብቶች መዳረሻ የነበረው እና የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ይፋ ሲደረግ ዕኩሌታ ተጫዋቾችን ያስመርጥ የነበረው ክለብ ፣ ከክለቡ ከመጀመርያ ተሰላፊዎች በተጨማሪ Squad player የሚባሉ ተጫዋቾች ጭምር የሚያስመርጠው ክለብ አሁን ላይ አንድ ተጫዋች ሳይስመርጥ መቅረቱ በጣም አሳዛኝ የታሪክ አጋጣሚ ነው።
እርግጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ከክዋክብት መር እሳቤ ፈቀቅ በማለት ከክለቡ የዕድሜ እርከን ቡድኖች በተገኙ እንዲሁም ከከፍተኛ ሊግ በሚደረጉ ዝውውሮች ቡድኑን ወደ መገንባት መሸጋገሩ ይታወቃል። በዚህም ክለቡ ከውጤት አንፃር ካጋጠመው መንሸራተት ባለፈ በስብስብ ጥራት ደረጃ ቡድኑ እንደቀደሙት ዓመታት ጠንካራ ስብስብ ባለቤት አለመሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። ነገርግን በዚህ ውስጥ ነጥረው የወጡ አዳዲስ ፊቶች መኖራቸው ግን አይካድም።
አሁን ለዓመታት የእግር ኳሳችን የከፍታ ማማ የነበረው ክለብ ስሙ ብቻ ቀርቷል። አሁን ወሳኙ ጥያቄ ይህ ክለብ እንዴት ይዳን ነው። ለዚህም ውይይት ብቸኛውና ብቸኛው መፍትሔ ነው።
ከዚህ ባለፈ ግን ሌሎች የሀገሪቱ ክለቦች ከዚህ ታሪካዊ ክስተት ምን ይማራሉ ነው ፤ ዛሬ በከፍታ የሚመላለሱ ሌሎች የሊጉ ቡድኖች ነገ ወደዚህ ዝቅታ እንዳይገቡ አሁን በደጉ ዘመን ምን መሥራት አለባቸው የሚለው ዓብይ ጉዳይ ነው።

የመጀመርያው ጉዳይ ዘላቂ የክለብነት ቅርጽ መያዝ፣ ቋሚ ገቢ መፍጠር፣ በችግር ጊዜ ክለቡን ከችግር ለማውጣት የሚታገል የልብ ደጋፊ መፍጠር እንደሚገባ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅታዊ ህመም ያስገነዝበናል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በባለጸጋው ሼህ መሐመድ አላሙዲን ኋላ ላይ በግዙፍ የኢንቨስትመንት ተቋማቸው ሚድሮክ ስፖንሰርነት ከ1980ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ለ15 ዓመታት የሀገራችን ፈርጣማ ክለብ እንደነበር እሙን ነው። ነገር ግን ይህን ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ በአግባቡ ሳይጠቀም በቢሾፍቱ ከተገነባው አካዳሚ በቀር ቋሚ ሀብት እና ከአፍሪካ ግዙፍ ክለቦች ጋር ቁመት የሚለካካ ክለብ የመሆን እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አሁን ላይ ከመንግሥት እና የልማት ድርጅቶች ካዝና በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት እየተመደበላቸው በደሞዝ እና የእለት ተእለት ወጪ ብቻ ገንዘብ እያባከኑ የሚገኙ ክለቦች የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ወይም የሚደጉማቸው ተቋም ፍላጎት ማጣት ሲመጣ በአንድ ጀንበር የማይከስሙበት ምንም ምክንያት የለም። ለዚህም ከወዲሁ መጻኢ እድላቸውን በራሳቸው ለመወሰን ጊዜው አሁን መሆኑን የቅዱስ ጊዮርጊስ ሁኔታ ሊያስተምራቸው ይገባል። ፈረሰኞቹ በ90 ዓመታት የገነቡት ጽኑ የደጋፊ መሰረት እና ወድቆ የመነሳት ታሪክ የጊዜው መርዘም ወይም ማጠር እንጂ መፈታቱ ላይቀር ይችላል። የከተማ እና የዞን ብሎም የድርጅቶችን በጀት ተንተርሰው የተቋቋሙ ክለቦች ጽኑ የደጋፊ መሠረት አለመጣላቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተደጋጋሚ ወድቆ የመነሳት ታሪክን ላይደግሙ እንደሚችሉ ከዚህ ቀደም ገናና የነበሩትና ላይመለሱ ከስመው የቀሩት ኮተን፣ ምድር ባቡር እና ሙገርን የመሳሰሉ ክለቦችን ማስታወስ ግድ ይላል። ከዘመናት በኋላ ራሳቸውን መልሰው ያገኙት መቻል፣ ኦሜድላ እና ንብ የመሳሰሉ ክለቦችም በቀደሙ ዘመናት የነበራቸው የደጋፊ እና የውጤት ታሪክ አሁን አለ ለማለት ያስቸግራል።
ቡድኖች የችግር ጊዜን ለማሳለፍ ከሚዘይዷቸው መላዎች አንዱ የወጣት እርከን ቡድኖቻቸውን በማጎልበት ለዋና ቡድናቸው ግብአት ማድረግ ነው። የቅርብ ዓመታት የባርሴሎና የፋይናንስ ውጥንቅጥን ተከትሎ ታላላቅ ኮከቦችን ለማስፈረም መቸገሩ በጥልቀት የክለቡ አካዳሚ ፍሬዎችን እንዲጠቀም አስገድዶታል። ቡድኑ በውጤት ደረጃ እንዲረጋጋ እና የፋይናንስ ቀውሱን እንዲሻገር የላ ማሲያ አስተዋጽኦ የማይተካ ሚና እየተወጣ ነው። ይህ ሞዴል በኛ ሀገር ሲተገበር ማየት ቅንጦት ይመስላል። ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድን ለመያዝ ክለቦች ፍላጎት አጥተው ፌዴሬሽኑ አስገዳጅ ህግ እስከማውጣት አድርሶታል። የወጣቶች ልማት ላይ ምንም በሚባል ደረጃ የማይሰሩ ክለቦቻችን ቢያንስ እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ጊዜያትን ለማለፍ ብቁ ወጣቶችን መጠቀም ይችሉ ነበር። በቅርብ ጊዜያት ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ወጣቶች ላይ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ሲሆን ከዚህ ቀደም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መብራት ኃይል፣ ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ሙገር ሲሚንቶ በገፍ ከወጣት ቡድን አሳድገው ውጤታማ ሲሆኑ ተመልክተናል። አሁን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተደራጀ የወጣት ልማት ሥራ ሠርቶ ቢሆን ይህ ወቅት ክለቡን ከመታደግ አልፎ እግር ኳሳችን አዳዲስ ከዋክብትን እንዲያስተናግድ መንገድ የሚከፍትልን ጥሩ አጋጣሚም ይሆን ነበር።
በጥቅሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ90 ዓመታት ታሪኩ በርካታ ከፍታዎችን እንዲሁም ዝቅታዎችን ያየ ጠንካራ ክለብ ነው። ከፋሺሽት ወረራ እስከ የመንግሥት ስርዓት ለውጥ ብዙ ያሳለፈው ስመ ገናናው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ላይ የተጋረጠበትን ችግር ተሻግሮ ወደ ቀደመው ክብሩ እንደሚመለስ ብዙሃኑ የእግር ኳስ ቤተሰብ ያምናል ፤ ይህ መሆኑም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ወሳኝ ነውና።

