የሁለተኛ ቀን የ24ኛ ሳምንት የሀዋሳ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና ተጋጣሚያቸውን አሸንፈዋል

አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
ኢትዮጵያ መድኖች አከታትለው ያስቆጠሯቸው ሁለት ፈጣን ጎሎች የጨዋታውን መልክ በቀየረው የሀዋሳ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በ13ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ ከማዕዘን ምት ራሱን ነፃ አድርጎ ከብሩክ የተቀበለውን የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ሁለት ተጫዋቾችን በማለፍ በግራ እግሩ በመምታት እጅግ አስደናቂ ጎል ማስቆጠር ችሏል።
በዚህች ጎል የተነቃቁት መድኖች የሚያገኙትን ክፍት ሜዳ በመጠቀም 16ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝን መነሻ ያደረገው ኳስ በግራ መስመር በፍጥነት የመጣው ያሬድ ካሳዬ ተቀብሎ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ በቀላሉ ወደ ጎልነት በመቀየር የመድኖችን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።
በአዞዎቹ በኩል በአንድ አጋጣሚ ፊሊፕ ጄሮም የግቡ የላይኛው ቋሚ ከመለሰበት ሙከራ በቀር እንደ ቡድን በተደራጀ እንቅስቃቃቄ አደጋ መፍጠር ሲቸገሩ ይሉቅንም ሦስተኛ ጎል አማኑኤል ኤርቦ ሊያስቆጥርባቸው ተቃርቦ የግቡ ግራ ቋሚ መልሶላቸዋል።

ከዕረፍት መልስ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ብልጫ የተወሰደባቸውን የመሐሉን የሜዳ ክፍል ለመቆጣጠር የተጫዋች ቅያሪ ቢያደርጉም የመድኖችን የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መውሰድ አልቻሉም። አዞዎቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም 84ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ተገኘ ጥሩ ሙከራን አድርጎ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ አድኖበታል።
አስቀድመው ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች መነሻነት ብዙም ጫና ያልነበረባቸው ኢትዮጵያ መድኖች በተረጋጋ ሁኔታ ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ በማስኬድ የሚፈልጉትን ሦስት ነጥብ አሳክተው 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፋዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከተማ
ጥሩ ፍክክር ባስመለከተን የምሽቱ ጨዋታ በ12ኛው ደቂቃ በመናፍ ዐወል ከተከላከይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ ራሱን ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ነፃ አድርጎ የወጣው አህመድ ሁሴን በጥሩ ሁኔታ ኳሱን ከፍ አድርጎ መረቡ ላይ በማሳረፍ አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል።
ብዙም ሳይቆይ ምላሽ የሰጠው ኢትዮጵያ ቡና 19ኛው ደቂቃ ላይ የተሰነጠቀለትን ኳስ ዘላለም አባተ የግብ ጠባቂው ናትናኤል ተፈራ ስህተት ታክሎበት ቡናማዎቹን ወደ ጨዋታው የመለሰች ጎል አስቆጥሯል። ተጨማሪ ጎል ፍለጋ የታተሩት ቡናማዎቹ 26ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አባተ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን በጥሩ መንገድ የላከውን በፍቃዱ አለማየሁ በድንቅ አጨራረስ ኳስና መረብን አገናኝቶ ኢትዮጵያ ቡና ከመመረታት ተነስቶ እንዲመራ አስችሎታል። ሙከራዎች ሁሉ ወደ ጎልነት በሚቀየሩበት በዚህ ጨዋታ 30ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ለራሱም ለቡድኑንም ሁለተኛ የአቻነት ጎል አስቆጥሯል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ ቢመስልም አልፎ አልፎ በሁለቱም በኩል ከሚደረግ ጥረት ውጭ የጠራ ሙከራ መመልከት አልቻልንም። ሆኖም ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ተቀይሮ የገባው ሀምዛ ሱልጣን በግንባሩ በመግጨት ቡናማዎቹን መሪ የምታደርግ ሦስተኛ ጎል አስገኝቷል። የጨዋታው መጠናቀቂያ 85ኛው ደቂቃ ላይ
የስታዲየሙ መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ከአስር ደቂቃዎች በላይ ተቋርጦ ሲጀምር አዳማ ከተማዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

