በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ቀይ ቀበሮዎቹን የሚገጥሙትና በ2025 በመድረኩ ያሳኩትን ክብር ለመድገም የሚያልሙት የአትላስ አናብስት የተመለከቱ መረጃዎች

የ2025 የውድድሩ ቻምፕዮን እና የቀጠናዊ ውድድር ‘UNAF’ ቻምፕዮኗ አስተናጋጅ ሀገር ሞሮኮ ውድድሩን የማሸነፍ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት አንዷ ናት። በ2025 ማሊን በመለያ ምት በማሸነፍ ያሳካችው የመጀመሪያ ዋንጫ ለመድገም ወደ ውድድሩ የቀረበችው ሞሮኮ ለዝግጅት እንዲረዳት የተሳተፈችበት በቅርቡ በሊቢያ አዘጋጅነት የተካሄደው የሰሜን አፍሪካ እግር ኳስ ህብረት ዋንጫ (UNAF) በበላይነት በማጠናቀቅ ቀጠናዊ የበላይነቷን ባረጋገጠችበት ማግስት ለታሪካዊ ተከታታይ ክብር ራሷ ወደ አዘጋጀችው ድግስ ቀርባለች።
ከአንድ ዓመት በፊት ሀገሪቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ካደረጉ አሰልጣኝ ናቢል ባሃ በመለያየት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቲያጎ ፔሬራ የሾመችው ሞሮኮ በሮያል ሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (FRMF) በሚመራውና የአስርት ዓመታት የወጣት ተጫዋቾች ልማት ‘ፕሮጀክት’ ታግዛ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ገንብታለች። በሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም በተካሄደው የውድድሩ መክፈቻና የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ ከቱኒዝያ ጋር 1 ለ 1 አቻ የተለያዩት የአትላስ አናብስት እንደ አብዛኞቹ የአህጉሪቱ ቡድኖች ጠጣር የተከላካይ ክፍል እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ አጨዋወት አላት።
‘TSG’ የተባለ ተቋም በ2025 ውድድር እና በ2026 የማጣሪያ ውድድሮች ባደረገው ጥናት አብዛኛቹ የአህጉሪቱ ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች በዋነኝነት ደግሞ ሞሮኮ እና ሴኔጋል መከላከል ላይ መሰረት ባደረገ የፈጣን ሽግግር አቀራረብ ምርጫቸው እንዳደረጉ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በሀገር ውስጥ ውድድሮች እና አካዳሚ ቆይታቸው ጎልተው የወጡ በርካታ ተስፈኛ ወጣቶች አካቷል። በቅርቡ በተካሄደው የሰሜን አፍሪካ እግር ኳስ ህብረት ዋንጫ (UNAF) የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሽልማትን ያገኘው አማካዩ ኢብራሂም ራባን የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ሲሆን በተጠቀሰው ውድድር በአራት ጨዋታ እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ግቦች ያስቆጠሩት አዳም ቡጋዚር እና ራሚ ሉክማኒም እንዲሁም የቼልሲው ራባጅ ኢብራሂም የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት መሳሪያዎች ናቸው።

