ዋልያዎቹ ለሁለተኛው የወዳጅነት ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዳቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ

ዋልያዎቹ ለሁለተኛው የወዳጅነት ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዳቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ

ከማላዊ ጋር ነገ ከሚያደርጉት ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ አስቀድሞ ዋልያዎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሲሰሩ የተጠናከረ ዘገባ እነሆ!

ባሳለፍነው ቅዳሜ በድሬደዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከማላዊ አቻው ጋር ያደረገውን የመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታ በድል ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ከሚያደርገው ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ አስቀድሞ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ከ10:50 ጀምሮ ጨዋታውን በሚያደርጉበት ሜዳ አከናውኗል።

– ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ለሚዲያ በተፈቀደው የመጨረሻው ልምምድ ወቅት ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች የተሳተፉ መሆናቸውን አይተናል።

– አንበሉ ያሬድ ባዬን በተመለከት ትናንት ለብቻው ተነጥሎ ፊዝዮቴራፒ መከታተሉን ገልፀን ነበር። በዛሬው ልምምድ ወቅት ሶከር ኢትዮጵያ እስከነበረችበት ደቂቃ ድረስ ከቡድኑ ጋር የማሟሟቅ ስራዎች ሲሰራ ብቻ ተመልክተናል።

– ያሬድ ባዬ ለነገው ጨዋታ ይኖራል ወይ የሚለውን ተከታትለን ወደ ኋላ መረጃውን ወደ እናንተ የምናደርስ የሆናል።

– የቡድኑ ተጫዋቾች በጥሩ መነቃቃት እና በመልካም ጤንነት ላይ ሆነው ልምምዳቸውን ሲሠሩ ተመልክተናል።

– አሰልጣኝ ዮሐንስ ድል ካደረጉበት የቅዳሜው ጨዋታው በኋላ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው ገልፀው “ያሸነፍነው በታክቲካል ዲሲፒሊን የተሻሉ በመሆናቸው” እንደሆነ በገለፁት መሠረት በነገው ጨዋታ ወቅት በአንድ አንድ ተጫዋቾች ላይ ለውጥ በማድረግ ውጤቱን በድል ለማጠናቀቅ ታክቲካል ስራዎችን ይሰራሉ ተብሎ ይታሰባል።

– ባሳለፍነው ቅዳሜ ያጫወቱት ጅቡቲያውያን ዳኞች መሐመድ ዲራነህ ጉዲ፣ ራቺድ ዋይስ ቡራሌህ፣ አብዱራህማን አህመድ እና ኢትዮጵያዊው አሸብር ሰቦቃ የነገውንም ጨዋታ የሚመሩት ይሆናል።

– የቀጥታ ስርጭት በተሻለ የምስል ጥራት ወደ ተመልካቾቹ ያደረሰው የድሬደዋ የመንግስት ኮሚኒኬሽን የነገውንም ጨዋታ ያስተላልፈዋል ተብሎ ይጠበቃል።

– ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ከጨዋታዎቹ መቀራረብ አኳያ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ የማይሰጡ መሆኑን አውቀናል።

ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ ነገ ምሽት 12:00 ሰዓት ላይ በድሬደዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።