ሪፖርት| ግብ አልባ የነበረው የአበባ ቢቂላ ስታዲየም የጨዋታ ውሎ

ሪፖርት| ግብ አልባ የነበረው የአበባ ቢቂላ ስታዲየም የጨዋታ ውሎ

በዛሬው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተደረጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ግብ ሳያስመለክቱን በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ሐዋሳ ከተማ

በመጀመሪያው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመውሰድም ሆነ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ አደገኛ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች ፍጹም ብልጫን ወስደው የተጫወቱበት ነበር። በተለይም በአንተነህ ተፈራ እና በወንድሰን በለጠ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ እጅግ አስቆጪና ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ወደ ሐዋሳ የግብ ክልል ሲሰነዝሩ ነበር። ይሁን እንጂ በአጋማሹ በሜዳ ላይ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው የሐዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰኢድ ሀብታሙ እነዚህን ግልጽ የሆኑ የግብ ዕድሎች በተከታታይ እና በአስደናቂ ቅልጥፍና ሲያድንባቸው እንደነበር ተስተውሏል። በስተመጨረሻም በዚሁ በግብ ጠባቂው ብርቱ ጥረትና ጽናት ታግዞ የሐዋሳ ከተማ መረብ ሳይደፈር የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ በባዶ 0ለ0 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ከእረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ሐዋሳ ከተማ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በኳስ ቁጥጥርና በፍሰቱ ረገድ የተሻለ የበላይነት ማሳየት የጀመሩ ሲሆን በዚህም በ52ኛው ደቂቃ ላይ ተባረክ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሞከረው እንዲሁም ብሩክ ያሬድ ከቅጣት ምት ባደረጋቸው እና የባህርዳሩ ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዱ ያዳናቸው ኳስ ለግብ እጅግ የቀረቡ ነበሩ። ይሁን እንጂ የሐዋሳ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ብዙም ሳይዘልቅ የቀረ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታውን የበላይነት ይዘው የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች የጨዋታውን ፍሰት በፍጥነት ወደ ራሳቸው በማምጣት በድጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመጠጋት ለግብ የሚሆኑ አደገኛ ሙከራዎችን መሰንዘር ቀጥለዋል።

በተለይም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩት የጣና ሞገዶቹ እጅግ ተጭነው ማጥቃታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ83ኛው ደቂቃ ላይ ታዳጊው በረከት ወርቁ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ በዕለቱ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው የሐዋሳው ግብ ጠባቂ ሰኢድ ሀብታሙ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል። ጨዋታው በፈጣን እልህ አስጨራሽ ጥቃት በቀጠለበት በ86ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አንተነህ ተፈራ ከቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል የወጣበት አጋጣሚ ለባህር ዳር እጅግ አስቆጪ ነበር። ይሁንና በሐዋሳው ግብ ጠባቂ ሰኢድ ሀብታሙ ብቃት ታግዞ የባህር ዳር ከተማዎች ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ አዳማ ከተማ

የወራጅነት ስጋት የተደቀነባቸውን ሁለቱን ክለቦች ባገናኘው የከሰዓቱ ተጠባቂ ፍልሚያ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተመጣጣኝ የሚባል የሜዳ ላይ ፉክክር የታየ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ከተጋጣሚ የሚሰነዘርን ድንገተኛ ጥቃት በመስጋት ጥንቃቄን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ ነበር። ይሁንና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመጠጋትና ክፍተቶችን በመፈለግ ረገድ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች የተሻለ ተነሳሽነት ያሳዩ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን ከሁለቱም ወገን የተመልካችን ቀልብ ሊስብ የሚችል ይሄ ነው የሚባል የጎላ የግብ ሙከራ ሳይመዘገብ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ በባዶ 0ለ0 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ከእረፍት መልስ በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች የማጥቃት ብልጫቸውን ይዘው የተመለሱ ሲሆን አብዛኞቹን የአጥቂ መስመር እንቅስቃሴዎቻቸውን ከግራ መስመር መነሻ በማድረግ ወደ መቐለ ግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲገሰግሱ ነበር። በዚህም በ61ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ ዘልቀው በመግባት አቡበከር ሳኒ ያመቻቸውን ኳስ አቤነዘር ሲሳይ ቢሞክረውም ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ በግቡ ቋሚ በኩል ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጥቃታቸውን ከግራ መስመር መሰንዘር የቀጠሉት አዳማዎች በ67ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታውንና ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ የመለሰበት እንዲሁም በ75ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ማራኪ ቅብብል አቡበከር ሳኒ የሞከረውና ለጥቂት በቋሚው በኩል የወጣበት አጋጣሚዎች የሚታወሱ ነበሩ። ይሁንና ጨዋታው ተጨማሪ አደገኛ ሙከራዎችንም ሳያስመልክተን ያለ ምንም ግብ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።