ሁለገቡ አጥቂ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል

ሁለገቡ አጥቂ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል

በኢትዮጵያ መድን ለአንድ ዓመት ቆይታ የነበረው ሁለገቡ አጥቂ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ ለመመለስ ተስማምቷል

አዳዲስ ተጫዋቾችንም በማስፈረምም ሆነ የነባር ተጫዋቾቻቸውን ውል በማራዘም ስራ የተጠመዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁን ደግሞ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የቀድሞ ተጫዋቻቸውን ዳግም አግኝተዋል። ወደ ፈረሰኞቹ ለመመለስ የተስማማው ደግሞ አጥቂው አማኑኤል ኤርቦ ነው። ለቀናት ካደረገው ድርድር በኋላ ከክለቡ ጋር ከስምምነት የደረሰው አማኑኤል ከደቂቃዎች በፊት ከትውልድ ከተማው አርባምንጭ ወደ አዲስ አበባ የመጣ ሲሆን በዛሬው ዕለት ቅድመ ስምምነት ፈርሞ የህክምና ምርመራውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአርባምንጭ ከተማ እግርኳስ የጀመረው እና
ለገጣፎ ለገዳዲን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደግ እራሱን ማስተዋወቅ የቻለው አማኑኤል በመቀጠል በቅዱስ ጊዮርጊስ ለሁለት ዓመታት መጫወት ችሎ ነበር። ዘንድሮ ለአንድ ዓመት በኢትዮጵያ መድን ቆይታ አድርጎ በሃያ ስድስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ ቆይታ ካደረገ በኋላም ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፈረሰኞቹ ቤት መመለሱ እርግጥ ሆኗል።