የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 23 ተጫዋቾች በመያዝ ዛሬ የ 12ኛ ቀን ልምምዱን አድርጓል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅቱን ከጀመረ ዛሬ የ12ኛ ቀን ልምምዱ አከናውኗል። በ2027 ለሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በአራት ቀን ልዩነት የምድቡን የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን ከሱዳን እና ከሴኔጋል አቻዎቹ ጋር የሚያደርገው በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሐሌ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ከአስራ አንድ ቀን በፊት ለ40 ተጫዋቾች ጥሪ አድርጎ ልምምድ መጀመሩ የሚታወስ ነው። በብሔራዊ ቡድኑ ዙሪያ ያሉት ወቅታዊ መረጃዎችም የሚከተሉት ናቸው።
– ከመጀመርያው ጀምሮ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መከካል የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ክለቡ ባቀረው ጥያቄ መሠረት ቡድኑን ያልተቀላቀሉ ሲሆን እንዲሁም በኲዌት ሊግ የሚገኙት ጋቶች ፓኖም እና ከንዓን ማርክነህ ደግሞ ከቡድኑ ጋር ዝግጅት ያልጀመሩ ተጫዋቾች ናቸው።
– ከሰሞኑን ደግሞ ከቡድኑ ስብስብ መካከል ነፃነት ገብረ መድህን በአፍሪካ ውድድር የሚሳተፈው ወልዋሎን ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ክለቡን በመቀላቀሉ ብሔራዊ ቡድኑ 30 ተጫዋቾች በመያዝ ዝግጅቱን እየሰራ ቆይቶ ነበር።
– ዛሬ ደግሞ ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣርያ ላይ ተሳታፊ የሆነው ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ሰባቱ የዋልያዎቹን ካምፕ ለቀው የአሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ናሽናል ካምፒንግ ተቀላቅለዋል።
– በአሁን ወቅት የዋልያዎቹ ስብስብ ከ40 ዝቅ ብሎ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ በዛሬ ዕለት በአዲስ አበባ ስታዲየም ረፋድ ላይ ልምምዱን ሲሰራ ሶከር ኢትዮጵያ በቦታው በመገኘት ለመከታተል ችላለች።
– አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሃሌ በሚታወቁበት የስልጠና መንገዳቸው የመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ለተጫዎቻቸው ታክሊካል ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በመቀጠል ቡድኑ የመመሟቅ ስራዎችን ሲከውን በተፈቀደችው ደቂቃ መመልከከት ችለናል።
– በቅርቡ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጥሪ የቀረበለት በቆሙ ኳሶች በርካታ ግቦች ያስቆጠረው ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ብሩክ ዘላለም ምንም እንኳን ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቢቀርብለትም በዛሬው ዕለት የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ጋር አብሮ ሲሰራ ተመልክተናዋል። ምን አልባትም በቅርቡ ናሽናል ካምፒንግ ይቀላቀላል ተብሎም ይጠበቃል።
– ቀደም ብለን ባጋራናቹህ ዜና መሰረት በጉዳት ምክንያት ከልምምድ ርቆ ከሚገኘው የሸገር ከተማው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ ውጭ 23 የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን ዝግጅታቸውን በመልካም ሁኔታ ሲከውኑ ተመልክተናል።
– በዝግጅቱ መሐል ዋልያዎቹ ከሀገር ውስጥ ክለቦች አልያም ከውጭ ሀገራት ቡድኖች ጋር
የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሰምተናል።
– ዋልያዎቹ ከሱዳን አቻቸው ጋር በደቡብ ሱዳኑ ጁባ ናሽናል ስታዲየም ዓርብ መስከረም 15 ቀን ምሽት 1:00 ላይ ጨዋቸውን ሲያደርጉ መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ/ም 10:00 ደግሞ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሴኔጋል ጋር ጨዋታቸውን ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።

