ሲዳማ ቡና የሚያካሂደው የቻምፕዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ለመምራት የተመደቡ ዳኞች ታውቀዋል

በካፍ ቻምፕየንስ ሊግ ሀገራችንን የሚወክለው የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና ከቻዱ ኤግሎንስ ጋር ያለበትን የካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታን የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል። ካፍ በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረገው ምደባ መሰረት ጨዋታው በላይቤርያውያን ዳኞች የሚመራ ሲሆን ኢማኑኤል ሜንሳህ ዋና ዳኛ ፣ ዋሽንግተን ዶሎ አራተኛ ዳኛ እንዲሁም ጆኤል ዶ እና ፍራንሲስ ባህ ደግሞ ረዳት ዳኞች ሆነው ተመድበዋል።
የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ሲዳማ ቡና ቅዳሜ ነሐሴ 30 30 ሺ ተመልካቾች መያዝ በሚችለው በቻዱ ስታድ ኦሊምፒክ ማርቻል ኢድሪስ ዴቢ ኢቶ የሚያከናውን ሲሆን የመልስ ጨዋታውን ደግሞ እሁድ መስከረም 3 በድሬዳዋ ስታዲየም የሚያከናውን ይሆናል።

