በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥመው ቡድን ታውቋል

ግብፅ የ2027 ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እንደምታስተናግድ ይታወቃል። በዚህ ስምንት ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ላይ ለመካፈል ደግሞ 42 ሀገራት በማጣሪያ ውድድሩ የሚካፈሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በመጀመሪያው የማጣሪያ ውድድር ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተደልድሏል።
በዛሬው ዕለት በግብፅ መዲና ካይሮ በሚገኘው የካፍ ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው ድልድል ከዩጋንዳ አቻው ጋር የተደለደለው ብሔራዊ ቡድናችን የመጀመሪያውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነም በቀጣዩ ዙር ከሞሮኮ ጋር ይጫወታል። የመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ በመስከረም አጋማሽ እንደሚካሄድም ታውቋል።
የማጣሪያ ውድድሩ ሦስት በሜዳ ከሜዳ ውጭ የሚደረጉ ጨዋታዎች ያጠቃለለ ሲሆን የማጣሪያ ውድድሩን ያለፉ ሰባት ቡድኖች እና አዘጋጅዋ ሀገር ግብፅ ጨምሮ ስምንት ቡድኖች በ 2027 ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ይሳተፋሉ፤ በአፍሪካ ዋንጫው ወደ ፍፃሜ የደረሱ ሁለት ቡድኖችም
አህጉሪቱን ወክለው በ2028 የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል።

