የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማለፍ ተስፋው እንዴት ነው ?

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማለፍ ተስፋው እንዴት ነው ?

በሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ሀገራችንን የወከለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን በተመለከተ ተከታዩን ጥንክር አዘጋጅተናል።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊውና ሀገራችንን በትልቁ አህጉራዊ የክለቦች ውድድር ለመወከል በምስራቅ አፍሪካ ዞን የማጣሪያ ፍልሚያ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድሩ በምድብ 2 ተደልድሎ ሁለት ጨዋታዎችን ማከናወኑ ይታወቃል። ባሳለፍነው ቅዳሜ የጂቡቲውን ኡጄኮ ገጥሞ ሜዳ ላይ ባሰለፋቸው ተጫዋቾች ልክ 11 ግቦችን በማስቆጠር ያሸነፈ ሲሆን የምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን ትናንትና አከናውኖ ደግሞ በዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ንግድ ባንክ የሚገኝበት ምድብ ሁለት ላይ ሦስት ቡድኖች የተደለደሉ በመሆኑ ባንክ የምድብ ጨዋታውን ያጠናቀቀ ሲሆን ይህ ዘገባ በተጠናከረበት ጊዜ ትናንት ካሸነፈው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር እኩል ሦስት ነጥቦች ይዞ በሰፊ የግብ ክፍያ ልቆ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከባንክ ጋር በነጥብ እኩሌታ የተቀመጠው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ቀሪ አንድ ጨዋታ ከኡጄኮ ጋር ያለው ሲሆን ያንን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ በስድስት ነጥቦች ምድቡን በበላይነጥ የሚያጠናቅቅ ይሆናል። ሶከር ኢትዮጵያም የውድድሩን ደንብ በስፍራው ከሚገኙ የሴካፋ የውድድር አመራሮች እንዲሁን ከካፍ የውድድር ባለሙያዎች በመቀበል የሀገራችን ተወካይ የሆነውን ንግድ ባንክ የማለፍ ተስፋ እንደሚከተለው ለማጣራት ሞክራለች።

በውድድሩ ደንብ መሰረት የሦስቱ ምድብ የበላይ ሦስት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፉ ሲሆን ከሦስቱ ምድቦች ደግሞ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው አንድ ቡድን ተጨማሪ አራተኛ ቡድን ሆኖ ግማሽ ፍፃሜውን ይቀላቀላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከካፍ ባገኘነው መረጃ መሰረትም በዞኑ ከተደረገው የምድብ ድልድል ምድብ አንድ ከምድብ ሁለት እና ሦስት በተለየ ሁኔታ አራት ቡድኖችን ስለያዘ ከሌሎቹ ሁለት ቡድኖች የተሻለ ጥቅም እንዳይኖር በሚል በምድቡ አራተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን ውጤት እንዲሰረዝና በምድቡ አራተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀው ቡድን ጋር የተመዘገቡ ሁሉም ውጤቶች እንደሚሰረዙ ተደንግጓል። ይህንን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት በምድቡ አራተኛ ደረጃን ይዞ የሚገኘው ቡድን የኤርትራው ደንደን ሲሆን ከሰዓታት በኋላ ከማፉዞ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። ይህ ቡድን በሁለቱም የምድብ ጨዋታው በዬ ጆይንት ስታርስ እና ራየን የተሸነፈ ሲሆን ዛሬም ወይ አቻ አልያም ሽንፈት የሚያስተናግድ ከሆነ ምድቡን በውራነት ማጠናቀቁን ያረጋግጣል። ይህንን ተከትሎም በህጉ መሰረት ከደንደን ጋር የተመዘገቡት የምድቡ ሁሉም ውጤቶች የሚሰረዙ ሲሆን የምድቡ ጊዜያዊ መሪ ዬ ጆይንት ስታርስ ካስመዘገበው ነጥብ ሦስት ሲቀነስ ሦስት እንዲሁም ራየን ካስመዘገበው አራት ነጥብ ሦስት ሲቀነስ አንድ ነጥብ ላይ ይቀመጣሉ። ሁለቱ ቡድኖች ደግሞ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ እርስ በርስ የሚጫወቱ ሲሆን መሸናነፍ ወይም አቻ አንዱን ቡድን ብቻ የምድቡ አንደኛ ሆኖ (ዬ ጆይንት ካሸነፈ 6 ነጥብ ራየን 1 ነጥብ ፤ ራየን ካሸነፈ 4 ነጥብ ዬ ጆይንት ደግሞ 3 ነጥብ ያገኛሉ) እንዲያልፍ ያደርገዋል። እነዚህ ውጤቶች ደግሞ በዚህ ምድብ ምርጥ ሁለተኛ እንዳይኖር ያደርገዋል (ዬ ጆይንት 3 ነጥብ ቢኖረውም ከባንክ የበለጠ የግብ ክፍያ የለውም)። ልብ እንዲባል የሚያስፈልገው ጉዳይ ይህ የሂሳብ ስራ ገቢራዊ የሚሆነው በዛሬው የ8 ሰዓት ጨዋታ ማፉዞ ከደንደን ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ድል ወይም አቻ ውጤት ካስመዘገበ ነው።

ከላይ በገለፅነው መሠረት በምድብ አንድ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ የሚያልፍ ከሌለ በምድብ ሦስት ደግሞ ያለውን የሂሳብ ስሌት እንመልከት። በዚህም ሁለቱንም የምድቡን ጨዋታ አከናውኖ ሦስት ነጥብ ብቻ ያስመዘገበው ሲምባ ኩዊንስ ምድቡን ሲመራ እርስ በርስ አንድ ጨዋታ የሚቀራቸው ኬኒያ ፖሊስ እና ቶፕ ገርልስ ሦስት እና ዜሮ ነጥብ በማግኘት ተከታታይ ተቀምጠዋል። በምድቡ ከሚቀረው የሁለቱ ጨዋታ ኬኒያ ፖሊስ ካሸነፈ ስድስት ነጥብ ይዞ አንደኛ ሆኖ በቀጥታ የሚያልፍ ሲሆን ቶፕ ገርልስ ካሸነፈ ደግሞ ሦስቱም ቡድኖች ሦስት ሦስት ነጥብ ይይዛሉ። እርስ በርስ ባለ ውጤት እና ጎሎች የምድቡ የበላይ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ቡድን ሲለይ ምርጥ ሁለተኛ የሚሆነው ቡድን ግን ከባንክ የተሻለ የጎል ክፍያ ስለሌለው በዚህ ምድብ ምርጥ ሁለተኛ የማይኖር ይሆናል።

ሲጠቃለል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ 8 ሰዓት ማፉዞ እና ደንደን በሚያደርጉት ጨዋታ ማፉዞ ጨዋታውን ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ በመጀመሪያው ጨዋታ ያስቆጠረው 11 ግቦች ጠቅመውት ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ የሚያልፍበትን እድል የሚያገኝ ይሆናል። በግማሽ ፍፃሜውም ዳግም ከካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር የሚፋለም ይሆናል። ከላይ ባስቀመጥነው እና እስካሁን በተመዘገቡ ውጤቶች መሰረትም ንግድ ባንክ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፉ ዕድል እጅግ የሰፋ መሆኑን መናገር ይቻላል።