ወቅታዊ መረጃዎች በሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን በኩል…

ወቅታዊ መረጃዎች በሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን በኩል…

የነገ የዋልያዎቹ ተጋጣሚ የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድንን በተመለከተ አሁናዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ሞክረናል።

በታንዛኒያ፣ ኬኒያ እና ዩጋንዳ በ2027 ለሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ 54 የአህጉራችን ሀገራት በምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። ዋልያዎቹም በምድብ 10 ከሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ እና ሱዳን ጋር ተደልድለው እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን ያደረጉ ሲሆን ሦስት ነጥቦችን በመያዝ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎችን በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ከእነዚህ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች መካከል ደግሞ ነገ በባህር ዳር ስታዲየም የሚደረገው የሞዛምቢክ ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነው።

የነገ ተጋጣሚያችን የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን የምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ ጨዋታዎችን መልካም በሚባል ውጤት አጠናቆ አራት ነጥቦችን ሰብስቦ የነበረ ሲሆን ባሳለፍነው አርብ ግን በሜዳው በኢትዮጵያ አቻው 1ለ0 ተሸንፏል። ይህ ሽንፈት መላው የሀገሬውን ሰው ያስደነገጠ ውጤት መሆኑ እሙን ሲሆን ቡድኑም በአራተኛ የምድብ ጨዋታው በእጁ ያለውን የማለፍ ተስፋ ላለማጣት ነገ ባህር ዳር ላይ እንደሚፋለም ይጠበቃል።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ባሉ መረጃዎች አሰልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ ከአርቡ ጨዋታ በኋላ ተጫዋቾች ከሽንፈቱ ድባቴ እንዲወጡ የእረፍት ጊዜ ሰጥተው ቤተሰቦቻቸውን እንዲጎበኙ እንዳደረጉ ተሰምቷል። ብሔራዊ ቡድኑ በትናንትናው ዕለት ከማፑቶ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ የመጣ ሲሆን ምሽት ላይም አዲስ አበባ ቢሌ አየር ማረፊያ ደርሷል። ልዑካኑ አዳሩን በመዲናችን ያደረገ ሲሆን ዛሬ ቀትር 6 ሰዓት ላይ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ባህር ዳር የሚያመራ ይሆናል።

በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ የደረሰው የልዑካን ቡድን 38 አባላት የያዘ ሲሆን ከጨዋታው ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ግን ሁለት ግለሰቦች ቀድመው ባህር ዳር እንደገቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዓርቡ ጨዋታ ያልነበረውና በፖርቹጋል ተወልዶ ለሞዛምቢክ እየተጫወተ የሚገኘው አማካዩ ጊማ ስብስቡን የተቀላቀለ ሲሆን ጥሩ ብቃት እንዳለው የሚነገርለት ይህ በአዘርባጃን ሊግ የሚጫወተው ተጫዋችም ለቡድኑ ጥሩ ጭማሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን በባህር ዳር በሚኖረው ቆይታ አባይ ማዶ አካባቢ በሚገኘው ናይል ቪው ሆቴል መቀመጫውን የሚያደርግ ሲሆን ከሰዓት ስፍራው ከደረሰ በኋላም አመሻሽ ላይ ነገ ጨዋታውን በሚያደርግበት ውቡ ባህርዳር ስታዲየም የመጀመሪያ እንዲሁም የመጨረሻ ልምምዱን የሚያከናውን ይሆናል። ከልምምዱ በኋላም የቡድኑ አሠልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ የቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።