ኢትዮጵያ ቡና እና ሀላባ ከተማ ነጥብ ተጋሩ

ኢትዮጵያ ቡና እና ሀላባ ከተማ ነጥብ ተጋሩ

በአብዩ አረጋሽ

ቡናማዎቹ እና በርበሬዎቹ ያፋለመው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ7ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ።

ዛሬ በ9፡00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ብልጫ ወስዶ ጥሩ አጀማመር ማድረግ ቢችልም የጠሩ ዕድሎች መፍጠር አልቻለም። የኋላ ኋላ ተሻሽለው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ሀላባ ከተማዎችም በተመሳሳይ በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ግን በ49ኛው ደቂቃ ዘላለም አባተ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገራትን ኳስ ታይባ ምቦኑዩምዋኒ በግንባር በመግጨት መረብ ላይ አሳርፎ ኢትዮጵያ ቡናን መሪ አድርጓል ።

ሀላባ ከተማ ግን መሪነቱን ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ አልፈቀዱም። በ55ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው ረጂም ሚፍታህ በሀላባ ከተማው እስራኤል ሸጎሌ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብነት በመቀየር ለቡድኑ የአቻነት ግብ አስቆጥሯል።

ከአቻነት ግቡ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ዳግም መሪነቱን ለመጨበጥ ጥረት ቢያደርጉም ኳስና መረብ ሳያገናኙ ጨዋታው በ1ለ1 አቻ ውጤት ተጠናቋል። ኢትዮጵያ ቡና በአመዛዡ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም ሀላባ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ከሜዳው ውጪ አንድ ነጥብ ማሳካት ችሏል።