በአብዩ አረጋሽ
ባህር ዳር ከተማ እና ወልዋሎ በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታድየም ያካሄዱት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ4ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የባህር ዳር ከተማ የተሻለ የኳስ ቁጥጥርና ተነሳሽነት የታየበት ቢሆንም ቀዳሚ መሆን የቻሉት ግን በአመዛኙ በመከላከል ላይ ባተኮረ አቀራረብ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ወልዋሎዎች ናቸው። በ38ኛው ደቂቃ በፍቃድ ከራሱ የግብ ክልል በመሬት ለመሬት ያቀበለውን ኳስ በየነ ባንጃ ወደ ፊት በመውሰድና ተከላካዮችን በማለፍ ከሳጥን ውጪ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። በዚህም ወልዋሎ 1-0 በመምራት ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ባህር ዳር ከተማ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫናውን አጠናክሮ በመቀጠል በ50ኛው ደቂቃ ስምኦን ማሩ በሽመልስ በቀለ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አንተነህ ተፈራ ወደ ግብነት በመቀየር ባህር ዳር ከተማን ወደ ጨዋታው መልሷል።

ከአቻነት ግቡ በኋላ ባህር ዳር ከተማ የጨዋታ ቁጥጥሩን በማስቀጠል የድል ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም ወልዋሎዎችም የመሪነቱን ውጤት ለመመለስ እንዲሁም በመከላከልና በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ ሙከራዎችን አድርገዋል። በመጨረሻም ሁለቱ ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በጨዋታው ባህር ዳር ከተማ በኳስ ቁጥጥርና በጨዋታ ብልጫ የተሻለ ብቃት ያሳየ ቢሆንም ወልዋሎ በተገኘውን ዕድል ወደ ግብነት በመቀየር ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች አንድ አንድ ነጥብ በመጋራት ጨዋታውን አጠናቀዋል።

