የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለው ራምኬል ሎክ ጫማውን ሳይሰቅል ወደ አሰልጣኝነቱ ዓለም ገብቷል

በመስመር አጥቂነት ከተመለከትናቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው እና ያለፉትን ሦስት ዓመታት ደግሞ ወደ ደቡብ ሱዳን በማምራት ለአልሜሪክ ቤንትዩ ሲጫወት የቆየው ራምኬል ሎክ ወደ አሰልጣኝንነ ህይወት መግባቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።
ተጫዋቹ በአንደኛ ሊግ ለሚሳተፈው ለትውልድ ሀገሩ ክለብ ኑዌር ዞን ለማሰልጠን በዋና አሰልጣኝነት መሾሙ ሲታወቅ ከቡድኑ ጋር በጋምቤላ ከተማ ቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ከቆየ በኋላም የፊታችን ሀሙስ ከአረካ ከተማ ጋር የመጀመርያ የምድብ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ዲላ ከተማ እንደሚያቀና ገልፆልናል።
ራምኬል ኳስን ለማቆም ገና እንደሆነ እና አሁን ዋና ዕቅዱ ክለቡ ኑዌር ዞንን በዚህ ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ ማገዝ እንደሆነ የገለፀ ሲሆን ዕቅዱ ተሳክቶ ክለቡ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድግ ከሆነ ተመልሶ ለዚሁ ክለብ ተጫዋች በመሆን እንደሚያገለግል ገልፆልናል። ከዚህ ቀደም የወሰደቸው መጠነኛ የአሰልጣኝነት ስልጠና መኖሩን አያይዞ ገልፆልናል።
ራምኬል ሎክ ከዚህ ቀደም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያሳካ ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ ሀምበሪቾ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ድሬዳዋ ከተማ ከተጫወተባቸው ክለቦች መካከል ሲሆኑ ወደ ደቡብ ሱዳን በማቅናትም በአል ሜሪክ ቤንትዩ ተጫውቶ ማሳለፉ ይታወሳል።

