ብሪያን ኦሞኒ ከጉዳቱ እያገገመ ይገኛል

ዩጋንዳዊው ኢንተርናሽናል ብራያን ኦሞኒ በኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ አርባንምንጭ ላይ ከአርባምንጭ ከተማ በተጫወተበት ጨዋታ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷበት ከሜዳ ተገልሎ ቆይቷል፡፡ እግሩ ሁለት ቦታ የተሰበረው የፊት መስመር ተሰላፊው ኦሞኒ ህክምናውን ከሚከታተልበት ናይሮቢ ኬንያ ሆኖ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጠር ያለቆይታ ከጉዳቱ እያገገመ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

“አሁን በጣም በጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለው፡፡ ጂም ውስጥ ለላይኛው አካሌ የሚጠቅሙኝን  ልምምዶችን ጀምሪያለው፡፡ የህክምና ውጤቴ እየተሻሻለ ከመጣ በቀጣዩቹ ሁለት ወይም ሶስተ ሳምንታት መሮጥ እጀምራለው፡፡” ይላል የቀድሞ የአዛም እና ፖርትላንድ ቲምበርስ አጥቂ፡፡

ፈረሰኞቹ ፕሪምየርሊጉን ለማሸነፍ አንድ ነጥብ ብቻ በቂው መሆኑን በመስማቱ መደሰቱን የሚናገረው ብሪያን በፕሪምየር ሊጉ ጊዮርጊስ ተፎካካሪ የለውም ለሚሉም አስተያየት አለኝ ይላል፡፡ “ጥሩ ፉክክር አለ ቢሆንም ጊዮርጊስ ከሌሎች ክለቦች በተሻለ ለሙሉ የውድድር ዘመኑ ጠንካራ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ተጫዋቾቹ የጊዮርጊስን ታላቅነን በደንብ ስለሚረዱ የክለቡን መለያ ለመልበስ ብቁ መሆናቸውን ለማሳየት ሁሌም ጠንክረው ይሰራሉ፡፡”

የሰርዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” ስብስብ ውስጥ ተካቶ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ለሃገሩ ዩጋንዳ የተጫወተው ብሪያን ክሬንሶቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ከ1978 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለማለፍ ጥሩ ግዜ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ “የዩጋንዳ ክሬንስ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገርግን ስራው ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም፡፡ እኔ እንደማስበው ከሆነ የመጨረሻ ጨዋታችን ማሸነፍ የግድ ይለናል፡፡ ከዛ በኃላ ማለፋችንን ወይም አለማለፋችን ማወቅ እንችላለን፡፡ እራሳችንን እንዳለፍን ቆጠረን ማሳሳት አይገባንም” ሲል ብሪያን ሃሳቡን አጠቃሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *