በአፍሪካ ሊጎች የሚገኙ ኢትዮጵያን በሳምንቱ መጨረሻ ከክለቦቻቸው ጋር ያሳለፉትን ውሎ የሶከር ኢትዮጵያው ኦምና ታደለ ቃኝቷቸዋል፡፡
ሽመልስ በቀለ
ለግብፁ ፔትሮጀት ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሃያሉ ክለብ ዛማሌክ ላይ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ሽመልስ ጨዋታው በተጀመረ በ26ተኛው ደቂቃ ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን የዛማሌኩ ግብ ጠባቂ ሞሃመድ አቡ ጋማል ጥፋት የታከለባት ግብ ነበረች፡፡ በጨዋታው ዛማሌክ 2ለ1 አሸንፏል፡፡ ሽመልስ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ቢያሳይም በ66ኛው ደቂቃ በደረሰበት የብሽሽት ጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ ሽመልስ ይህ ዛማሌክ ላይ ያስቆጠረው 2ኛው ግብ ነው ፤ በ3 ጨዋታ ደግሞ 2ኛ ግቡ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ በቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ዛማሌክ ላይ ግብ ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=Mk2BzBhop0I
ሸመልስ ዛማሌክ ላይ ያስቆጠረው ግብ
ሳላዲን ሰኢድ
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ሳላዲን ሰዒድ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ለክለቡ አል አህሊ ባሳለፍነው ቅዳሜ ተሰልፎ ሙሉ 90 ደቂቃ ተጫውቷል፡፡ አልአህሊ የቀይ ባህር ዳርቻ አከባቢ የሚገኘውን ኤል ጉናን 2ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ የአጥቂ መስመሩን መርቷል፡፡ ሳላ በጨዋታው ግብ ባያስቆጥርም የተሻለ ተንቀሳቅሷል፡፡ የፊታችን ሀሙስ የሳለዲኑ አልሃሊ ከ ሽመልስ በቀለው ፔትሮጀት የሚጫወት ይሆናል፡፡
ኡመድ ኡኩሪ
የአምናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮኮብ ግብ አግቢ እና ተጫዋች የነበረው ኡመድ ኡኩሪ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ታውቆል፡፡ ለኢቲሃድ አሌክስአንደሪያ በአጥቂነት ላለፉት 4 ወራት የተጫወተው ኡመድ ግብፅን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡ ኡመድ ክለቡ አሌክስአንደሪያ ለ4 ወራት ያህል ደሞዝ ሳይከፍለው መቆየቱን የተናገረ ሲሆን ከክለቡ የለቀቀበት ምክንያትም ይህ አንደሆነ አስረድቷል፡፡ ለካፍ እና ለአለማቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ጉዳዪን ያመለከተው ኡመድ ቀጣይ ማረፊያው ሰሜን አፍሪካ ወይንም አውሮፓ ሊሆን እንደሚችል ታውቆል፡፡ ኡመድ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ለአሌክስአንደሪያው ክለብ የፈረመው በ2006 ክረምት ነበር፡፡
አበባው ቡታቆ
ኢትዮጵያዊው የግራ ተመላላሽ ተጫዋች የሆነው አበባው ቡጣቆ ለሱዳኑ አል ሂላል ባሳለፍነው ቅዳሜ በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ አበባው በአዲሱ ክለቡ 27 ቁጥር የሚለብስ ሲሆን፤ ለቅድመ ዝግጅት ኳታር የሚገኘውን አል ሂላልን የተቀላቀለው በ2007 ነበር፡፡
አህሊ ሼንዲ
የአህሊ ሼንዲ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ኮከቡ አዲስ ህንፃ እየተመራ የአዲሱን የውድድር ዘመን ዝግጅት ከጀመሩ ሰንትበት ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ አምና በጊዜያዊነት የተረከቡትን ቡድን በቋሚነት ተረክበው በግብፅ ቡድኑን እያዘጋጁ ሲሆን ናይጄርያዊው ኬሊቺ ኦሱኖዋን ጨምሮ ጠንካራ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡ በተያያዘ የቀድሞው የአዳማ ከነማ ኮከብ አብይ ሞገስ አህሊ ሼንዲን ለቆ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ማምራቱ ይታወሳል፡፡
ጌታነህ ከበደ
በደቡብ አፍሪካው የአብሳ ፕሪምየር ሺፕ እየተወዳደረ የሚገኘው ቤድቬስት ዊትስ አጥቂ የሆነው ጌታነህ ከበደ በክለቡ የተሰላፊነትን ቦታ ማግኘት ተስኖታል፡፡ ጌታነህ ከህዳር ወር ጀምሮ አንድም ጨዋታ ቋሚ ሆኖ ጀምሮ አያውቅም፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ ጋቭን ሃንት የጌታነህ ችግር ቋንቋ ሞሆኑን ሲናገሩ መደመጣቸው የሚታወስ ነው፡፡ የጌታነህው ዊትስ በሊጉ ከካይዘር ቺፍስ ቀጥሎ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ካፕ ደግሞ ከስወዚላንዱ ሮያል ሊዮፓርድስ ጋር ተደልድሏል፡፡