በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ራሱን ከእግርኳስ ተጫዋችቸነት ያገለለው ሙሉጌታ ምህረትን በክብር ለመሸኘት የመሸኛ ጨዋታዎች እንደሚዘጋጁ ዛሬ በሃዋሳ ሴንትራል ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ተደርጓል።
የሽኝት ጨዋታው አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ከሆኑት መካከል አቶ ሲሳይ አድርሴ ስለ ዝግጅቱ ሲናገሩ “ዋና አላማችን በእግር ኳስ ያገለገሉንን ባለውለታዎቻችንን ለማመስገን እና እንደዚህ አይነት ዝግጅቶችን በሃገራችን ለማስለመድ ነው። ብዙዎቻችን እንደምናቀው ሙሉጌታ ምህረት በሀገርም ሆነ በክለብም ደረጃ ብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪዋችን አስደስተዋል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ባለውለታችን አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን ተመካክረን በአራት ቡድኖች መካከል ሁለት ጨዋታዎችን አድርገን አሸናፊ የሆኑ ቡድኖችን ዋንጫ ለመሸለም ነው ያቀድነው”ብለዋል፡፡
አቶ ሲሳይ ስለሚሳተፉት ቡድኖች እና ጨዋታው ስለሚካሄድበት ቀን ጨምረው ሲያስረዱ “የሚሳተፉትን ቡድኖች ለመምረጥ አልተቸገርንም፡፡ ሁላችሁም እንደምታቁት ሙሉጌታ ለሶስት ክለቦች ተጫውቷል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ቡድኖች በቀጥታ አስገብተን አንዱን ቡድን ግን በእጣ እንዲወጣ አድርገን መርጠናል፡፡ ስለዚህ ውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ቡድኖች ሃዋሳ ከተማ ፣ ደደቢት ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ናቸው” ብለዋል፡፡
ሌላኛው የአዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት የሃዋሳ ከተማ የወጣቶች እና ስፖርት ሀላፊ እና የሃዋሳ ከነማ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ታሪኩ በሰጡት አስተያየት ሙሉጌታን አሞካሽተዋል፡፡ “ከሙሉጌታ ከምንም በላይ የሚገርመኝ የመምራት ብቃቱ ነው፡፡ በተለይ አሁን የያዘው ወጣቶችን የመምራት እና የማሳደግ ስራ ለክልሉ እግር ኳስ እድገት ጠቀሜታ አለው።” ብለዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ለረጅም ጊዜ ሀዋሳ ከተማን ያሰለጠኑት አንጋፋው አሰልጣኝ ከማል አህመድ ለሙሉጌታ እና ለአዘጋጅ ኮሚቴው ያላቸውን አክብሮት ገልፀው ከዚህም በኃላ እንደዚህ አይነቱ ተግባር እንዲቀጥል ተናግረዋል፡፡
