ኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 አመት በታች የማጠቃለያ ውድድር በወንዶች ፍፃሜ የሚጠበቁ ተጫዋቾች

ኮፓ ኮካኮላ ከ15 አመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ደቡብ ከ አማራ በሚያደርጉት የወንዶች ፍፃሜ ጨዋታ ይጠናቀቃል፡፡

በፍፃሜው የአማራው የግራ መስመር ተከላካይ ሞላዬ አከለ እና የደቡቡ የመስመር አጥቂ እስጢፋኖስ ዘውዴ የሚያደርጉት ፉክክር የሚጠበቅ ነው፡፡

PicsArt_1472919243719

 ዲላ ከተማ የተወለደው እስጢፋኖስ ዘውዴ የኮፓ ኮካኮላ ከፍተኛ ግብ አግቢነትን በ4 ግቦች እየመራ ይገኛል፡፡ ወደፊት የተሟላ ተጫዋች እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ታዳጊም ነው፡፡ ፈጣን እና ከመስመር እየተነሳ አደገኛ የግብ እድሎችን መፍጠር የሚችል ሲሆን ከከተማው ወጥቶ የሃገሪቱ ጀግና ለመሆን እንደበቃው ጌታነህ ከበደ ግብ የማነፍነፍ ተሰጥኦ ያለው ታዳጊ ነው፡፡ የሚያደንቀው እና ወደፊት መሆን የሚፈልገውም ቡኖ ከሚባለው በከተማው የሚገኝ ሰፈሩ እንደተገኘው ጌታነህ ከበደ ነው፡፡

በዲላ ከተማ ከሚገኘው ፋሪስ ትምህርት ቤት የተገኘው የ14 አመቱ እስጢፋኖስ የድንቅ ተሰጥኦ ባለቤት ቢሆንም ታዳጊነቱ ለብቻው ገኖ እንዲወጣ አላጓጓውም፡፡ ” እስጢፋኖስ ችሎታውን ለቡድኑ ጥቅም የሚያውል ተጫዋች ነው” ሲል የቡድኑ አሰልጣኝ ያሞካሸዋል፡፡ እርሱም ሰለ ፍጻሜው ጨዋታ ሲናገር ከግሉ ይልቅ ለጠንካራ የቡድን መንፈስ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ትረዳላትሁ፡፡ ‹‹ለውጤታማነት ወሳኙ ነገር ጠንካራ የቡድን መንፈስ ነው፡፡ እንደ ቡድን ከተጫወትን ከማሸነፍ የሚያቆመን ነገር የለም››

PicsArt_1472918028577

ሞላዬ አከለ ለአማራ ቡድን ከግራ መስመር ተከላካይም በላይ ነው፡፡ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ እና የግብ እድሎች ምንጭ ነው፡፡

በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ አማራ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ማሸነፍ ብቻ አላማ አድርጎ ከኢትዮ ሶማሌ ጋር ተጫወተ፡፡ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘት የሚበቃቸው ኢትዮ ሶማሌዎች በአቻ ውጤት ከማጠናቀቅ ያገዳቸው የሞላዬ የቅጣት ምት ጎል ነበር፡፡

በግማሽ ፍጻሜው የውድድሩን ጠንካራ ቡድን ኦሮምያን እንዲያሸንፉም የሞላዬ በሜዳ ውስጥ መኖር ወሳኝ ነበር፡፡ ለመጀመርያው ጎል መቆጠር ምክንያት ሲሆን በጨዋታውም ድንቅ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡

ወልድያ ከተማ የተወለደው ሞላዬ ወደ ኮፓ ኮካኮላ ውድድር የመጣው በወልድያ ት/ቤት ባሳየው አቋም ነው፡፡ ተካልኝ ደጀኔን የሚያደንቀው ሞላዬ ወደ ፊት በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የመሆን ህልም አለው፡፡ በወልድያ ስፖርት ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው ታላቅ ወንድሙ ሙሉቀን አከለን ፈለግ ተከትሎም በክለብ ደረጃ መጫወትን ያልማል፡፡  አሰልጣኙም ‹‹በቅርብ አመታት በክለብ እግርኳስ እናየዋለን›› ሲሉ ተስፋ ጥለውበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *