ዋሊያዎቹ ሲሼልስን በማሸነፍ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያውን አጠናቀዋል

በ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሲሼልስ አቻውን ዛሬ በሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም አስተናግዶ 2-1 በማሸነፍ የማጣሪያ ውድድሩን በድል ማጠናቀቅ ችሏል።

ዋሊያዎቹ ወደ ጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ በጥሩ ሁለተኛነት ለማለፍ ያላቸውን የጠበበ ዕድል ለመጠበቅ በሰፊ ግብ ተጋጣሚያቸውን ለማሸነፍ አቅደው ወደሜዳ የገቡ ቢሆንም በጨዋታው ዝቅተኛ ግምት በተሰጣቸው ሲሼልሶች ተፈትነዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታው ከመጀመሩ አንስቶ በማጥቃት በመጫወት ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ችሏል። በ5ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከስዩም ተስፋዬ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የሲሼልሱ ግብ ጠባቂ ጂኖ ሜላንቴ እንደምንም ያወጣበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። ዋሊያዎቹ ኳስን ተቆጣጥሮ በህብረት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመግባት ሲሞክሩ ሲሼልሾች በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።

ጨዋታው በተጀመረ በ20ኛው ደቂቃ አቺሌ ሄንሪቴ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ሲሼልስን መሪ ማድረግ ችሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም መደናገጥ ሳይፈጠርበት አቻ የሚያደርገውን ግብ ለማግኘት አጥቅቶ መጫወቱን የቀጠለ ሲሆን በ33ኛው ደቂቃም በጌታነህ ከበደ ግብ አቻ ለመሆን ችሏል። ግቡ ጌታነህ ከበደ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሊያ ባደረጋቸው 6 የመጨረሻ ጨዋታዎች ያስቆጠረው 8ተኛ ግብ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድርን በ6 ግቦች በኮከብ ግብ አግቢነት እንዲመራ ያስቻለውም ሆኗል።

2

በሁለተኛው አጋማሽ አሠልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ በሃይሉ አሠፋን በሺመክት ጉግሳ ቀይረው በማስገባት ቡድናቸው ተጭኖ በመጫወት ተጨማሪ ግብ እንዲያስቆጠር ሲገፋፉ ተስተውለዋል። በ53ተኛው ደቂቃ የሲሼልሱ ግብ ጠባቂ ጂኖ ሜላንቴ በሳልሃዲን ሰዒድ ላይ በሰራው ጥፋት ምክኒያት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሳልሃዲን ወደግብነት በመቀየር ኢትዮጵያን መሪ አድርጓል።

ሳልሃዲን ሰዒድ ከግቡ መቆጠር በኋላ ተደጋጋሚ አጋጣሚዎችን ማግኘት ቢችልም ዕድሎቹን በአግባቡ መጠቀም አልቻለም። ኤፍሬም አሻሞ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ስዩም ተስፋዬ በዋሊያዎቹ በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ተጫዋቾች ነበሩ።

ጨዋታው በ2-1 ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን ውጤቱም አሠልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ቡድኑን በጊዜያውነት ከተረከቡ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ሁለተኛ ድል ሆኖ ተመዝግቧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ 11 ነጥብ እና በ3 የግብ ዕዳ ምድቡን በሁለተኛነት ማጠናቀቅ የቻለ ሲሆን ወደ 2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ በጥሩ ሁለተኛነት ለማለፍ በሚደረገው ውድድር ከቤኒን በመቀጠል በሁለተኛነት ተቀምጧል። ቡድኑ ወደ ጋቦን ለመጓዝም የቱኒዚያ፣ ኡጋንዳ፣ ሴንትራል አፍሪካ፣ ኬፕ ቨርዴ እና ስዋዚላንድን መሸነፍ ይጠብቃል።

 

 

CH

ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ይህንን ዘገባ ወደ እናንተ እንዲደርስ እገዛ ስላደረገ እናመሰግናለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *