በ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡ የወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከነማ አሰልጣኙ ታረቀኝ አሰፋን ማሰናበቱ ተነግሯል፡፡
የ2 ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኑ ሀዋሳ ከነማ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከፍተኛ ገንዘብ ካፈሰሱ ክለቦች አንዱ ቢሆንም በአሰጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ‹‹ ዳኜ ›› ስር ከ11 ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ማግኘት የቻለው 7 ነጥቦችን ብቻ ነው፡፡
የቀድሞው የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ባለፈው ክረምት ከጎንደሩ ክለብ ዳሽን ቢራ ጋር ከስምምነት ደርሰው የነበረ ቢሆንም ሀዋሳ ከነማ ሳይፈቅድ በመቅረቱ ዝውውሩ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡
አሰልጣኝ ታረቀኝ ባለፈው የውድድር ዘመን አጋማሽ የተረከቡት ቡድን ውጤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆሉ ለስንብታቸው እንደምክንያት የተገለፅ ሲሆን አምና ቡድኑን ለ6 ወራት ይዘውት የነበሩት አሰልጣኝ በፍቃዱ ዘሪሁን ቡድኑን በጊዜያዊነት ሊረከቡ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ሀዋሳ ከነማ ከ1995 በኋላ መጥፎውን የውድድር ዘመን እያሳለፈ ሲሆን በአሰልጣኝ ታረቀኝ ስር ካደረጋቸው 23 ጨዋታዎች ሙሉ 3 ነጥቦችን ማገኘት የቻለው በ5 ጨዋታዎች ብቻ ነው፡፡
የ2007 የውድድር ዘመን ከተጀመረ ወዲህ ወልድያ እና ደደቢት አሰልጣኞቻቸውን ያሰናበቱ ሰሲሆን ሀዋሳ ሶስተኛው ክለብ ሆኗል፡፡