የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አስመዝግቧል

 

በአምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታድየም ላይሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ኢትዮጽያ ቡና 2-1 በማሽነፍ የአመቱን የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና በ 4-3-3 አሰላለፍ ወደሜዳ ሲገባ ከግብ ጠባቂው ሀሪስተን ሄሱ ፊት ኤፍሬም ወንድወሰን እና ኤኮ ፌቨርን በመሀል ተከላካይነት እንዲሁም አብዱልከሪም መሀመድ እና አህመድ ረሽድ በቀኝና ግራ ተከላካይነት ተጠቅሟል። እንዲሁም መሀል ሜዳ ላይ ከተከላካይ አማካዪ ጋቶች ፓኖም ፊት ኤልያስ ማሞን እና አማኑኤል ዮሀንስን ሲያጣምር በሣዲቅ ሤቾ በሚመራው የፊት መስመር ላይ  ያቡን ዊልያምን እና ሳሙኤል ሳኑሚን በግራና ቀኝ የመስመር አጥቂነት አሰልፏል።

የአለማየሁ አባይነሁ ሲዳማ ቡና በበኩሉ  ለአለም ብርሃኑን በግብ ጠባቂነት ሲያስገባ በ 4-1-3-2 ቅርፅ ሳውሬል ኦልርሺ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ አበበ ጥላሁን እና ሳንደይ ሙቱኩን ከቀኝ ወደግራ በተከላካይ መስመር እንዲሁም  ሙሉአለም መስፍንን በተከላካይ አማካይነት ሲያሰልፍ ከ ሙሉአለም ፊት ትርታዬ ደመቀ ፣ ፍፁም ተፈሪ እና ወሰኑ ማዜን ከ ሁለቱ የፊት አጥቂዎች አዲስ ግደይ እና ኤሪክ ሙራንዳ ጀርባ ተጠቅሟል።

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወደ ሲዳማዎች ሜዳ አድልቶ ሲጀመር በ9ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ አህመድ ረሻድ ወደ ተጋጣሚው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ኳስ ይዞ በመግባት ከሳውሬል ኦልርሺ ጋር አንድ ለአንድ ተገኛኝቶ ለማለፍ ጥረት ሲያደርግ በኦርሊሽ ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሳሙኤል ሳኑሚ በ10ኛው ደቂቃ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ከግቡ መቆጠር በኃላ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሲዳማዎች ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም ግን ቡድኑ የመሀል ሜዳ የበላይነቱን ከተጋጣሚው መንጠቅ አልቻለም።  የአጥቂ አማካዮቹም የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎቹ ማድረስ ተስኗቸው ታይተዋል። በተጨማሪም የሲዳማ ቡና አማካዮች የተጋጣሚያቸው አማካዮችም ኳስ ሲይዙ ምቾት እንዳይሰማቸው እና አደጋ ሚፈጥሩ ኳሶችን እንዳያሻግሩ በማረግ በኩልም ተዳክመው ታይተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽም አዲስ ግዳይ በግሉ ካረገው እንቅስቃሴ በተለይም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም በወሰኑ መዐዜ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በግምት ከግቡ 20 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት መቶ ግብ ጠባቂው ከያዘበት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሌላ ሲዳማዎች አስፈሪ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ ከሆኑበት ጎል በኃላ በግራ መስመር በሳሙኤል ሳኑሚ በኩል ያደላ ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በተለይም በ15ኛው ደቂቃ ላይ ሳኑሚ ከመሀል ሜዳ ከኤልያስ ማሞ የተሻገረለትን ኳስ ይዞ በመግባት ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ባልተጠበቀ ሁኔታ ያመከነበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነበር። ይህ በመልሶ ማጥቃትም ጭምር የሚታገዝ የኢትዮጽያ ቡናዎች የግራ መስመር ጥቃት ቀጥሎ በ23ኛው ደቂቃ  አሁንም ሳሙኤል ሳኑሚ በፍጥነቱ ተጠቅሞ በግራ በኩል ወደውስጥ ይዞ የገባውን  ኳስ ለቀኝ መስመር አጥቂው ያቡን ዊልያም አሻግሮለት ያቡን ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

picsart_1481401434483

ከጎሉ መቆጠር አራት ደቂቃዎች  በኃላ ሲዳማዎች ሳንደይ ሙቱኩን ከግራ መስመር ተከላካይነት በቀኝ በኩል ወዳለው የመሀል ተከላካይነት በማምጣት እና ቀድሞ ቦታው ላይ የነበረውን አንተነህ ተስፋዬን ወደቀኝ መስመር ተከላካይነት በመውሰድ የሳሙኤል ሳኑሚን ጉልበት እና ፍጥነት ለመቋቋም ሙከራ አድርገዋል። ሆኖም ግን ከአማካይ መስመር ተሰላፊዎች በቂ ሽፋን ማግኘት ያልቻለው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል የተጠበቀውን ያህል መጠናከር አልቻለም።

የሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ወሰኑ መዐዜን ወደግራ መስመር ተከላካይነት በመመለስ ፀጋዬ ባልቻን በአንተነህ ተስፋዬ ቀይረው የገቡት ሲዳማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና መፍጠር ችለው ነበር። ፀጋዬም ከቀኝ መስመር በመንሳት ለቡድኑ መነቃቃት ቁልፍ ሚና መወጣት ችሎ ነበር። በ54ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት የላከለትን ኳስ አዲስ ግደይ ሲተውለት ፍፁም ተፈሪ የቡናው ተከላካይ ኢኮ ፌቨር ለማውጣት ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር አግኝቶ ጎል አድርጓታል። እንዲሁም በ57ኛው ደቂቃ አሁንም ፀጋዬ ባልቻ ያሻማውን ጥሩ ኳስ ኤሪክ ሙራንዳ እና አዲስ ግደይ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ከዚህ በኃላ ሲዳማዎች ይበልጥ ወደጨዋታው ይመለሳሉ ተብሎ ቢጠበቅም በመጀመሪያው ግማሽ ወደተወሰደባቸው የመሀል ሜዳ ብልጫ ተመልሰዋል። ቡድኑም በረጅም ኳሶች ለአጥቂዎች እድል ለመፍጠር ቢሞክርም ውጤቱን ለመቀየር ሚያበቃ አጋጣሚ ግን መፍጠር አልቻለም።

ግብ እንደተቆጠረባቸው በ55ኛው ደቂቃ እያሱ ታምሩ በሳዲቅ ሴቾ ቀይረው ያስገቡት ኢትዮጽያ ቡናዎች ሳሙኤል ሳኑሚን ብቸኛ የፊት አጥቂ አርገው አማኑኤል ዮሀንስን ከጋቶች ፓኖም ጋር ከተከላካዮቹ ፊት በማጣመር ተቀይሮ የገባውን እያሱ ታምሩ ከኤልያስ ሞሞ እና ከያቡን ዊልያም ጋር በአጥቂ አማካይነት አዋቅረው በ 4 2 3 1 ቅርፅ ጨዋታውን በተጨማሪ ጎል ለመጨረስ ተጭነው ተጫውተዋል። በፈጠሩትም ጫና በ64ተኛው ደቂቃ የሲዳማውን ግብ ጠባቂ ለአለም ብርሀኑ ስህተት ተጠቅሞ አማኑኤል የሰጠውን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ ለማስቆጠር ሲሞክር የመሀል ተከላካዩ አበበ ጥላሁን ያወጣበትን ሙከራ ጨምሮ ሌሎች ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል።

ሌላው የቡድኑ ለውጥ በ70ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ ወጥቶ ሳለአምላክ ተገኝ ሲገባ እና የቀኝ መስመር ተከላካይነቱን ቦታ ሲይዝ የታየ ነበር። በዚህ ቅያሪ መሰረት የቀኝ መስመር ተከላካይ የነበረው አብዱልከሪም መሀመድ ወደመሀል በመጠጋት እና ከጋቶች ጎን በመሆን ቀሪውን ሀያ ደቂቃዎች ጭርሷል። የፊት አጥቂነቱንም ኤልያስ ሞሞ ተረክቧል። የአብዱልከሪምን የቦታ ለውጥ እና የተጨዋቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ተከትሎም ቡናዎች ይበልጥ በጨዋታው ላይ የበላይ መሆን ችለው ታይተዋል ። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ኢትዮጵያ ቡናዎች  በአማኑኤል ዮሀንስ ፣ በኤልያስ ማሞ እና በአብዱልከሪም መሀመድ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። ነገር ግን ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ባይችሉም ውጤታቸውን በምስጠበቅ አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡

 

አስተያየቶች

picsart_1481401621437

አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሴቪች – ኢትዮጵያ ቡና

” ጨዋታው ለኛ በጣም ከባድ ነበር ።  በጨዋታው ማጥቃት ላይ አመዝነን በሶስት አጥቂዎች በመጫወታችን ደስተኛ ነኝ። እንዳያችሁትም ዛሬም እንደ አዳማው ጨዋታ ሁሉ አምስት እና ስድስት የሚደርሱ ጥሩ የጎል እድሎችን ፈጥረን ነበር። ማግባት የቻልነው ግን ሁለቱን ብቻ ነው ”

” ሲዳማ ቡና ጥሩ እና ጠንካራ ቡድን ነው ጎል አስቆጥረው የመጨረሻውን ሀያ ደቂቃ ከባድ አድርገውብን ነበር ።”

” ቀጣዩ ጨዋታችን ከወላይታ ድቻ ጋር ነው። ከሁለት ወር በፊት በወዳጅነት ጨዋታ ገጥመናቸዋል። ጠንካራ ቡድን አላቸው። ለኔ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ መጫወት ተመሳሳይ ነው ። ሁሌም ለማሸነፍ ነው መጫወት ያለብን ”

” አብዱልከሪም እግርኳስን በሚገባ የሚያውቅ እና ፈጣን ተጨዋች በመሆኑ በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ወደመሀል አምጥተነዋል። ጥሩም ተንቀሳቅሷል። ”

picsart_1481401560366

አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

” በእንደዚህ አይነት ድባብ እግር ኳስን መጫወት ያስደስታል ”

” በመጀመሪያው እስር ደቂቃ በሰራነው በረሳችን ስህተት ጎል ተቆጥሮብናል ጨዋታው ሲጀመር ፈጥነውብንም ስለነበር ልጆቼ መረጋጋት አልቻሉም ነበር ። ላረጋጋቸውም ሞክሬም በነበረው ከፍተኛ ድምፅ ምክንያት መደማመጥ አልቻልንም ነበር። መልበሻ ቤት ስንገናኝ ግን የነበሩብንን ክፍተቶች ተነጋግረናል በተለይ ተከላካይ መስመሩን ወደፊት በማስጠጋት እና አጥቂ በመጨመር ጨዋታውን ለመቀየር ሞክረናል”

” መሀል ላይ የቡና እንቅስቃሴ ስለሚበልጥ በቁጥርም ስለሚበዙ እና ብዙ ኳሶችንም ስለሚነካኩ ብልጫ ተወስዶብን ነበር ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ረጅም ኳሶችን በመጠቀም ለማስተካከል ሞክረናል”

” በዳኝነቱ ላይ ብናገርም ለውጥ ስለማይመጣ ብዙ መናገር አልፈልግም፡፡ ነገር ግን የፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል”

“ስለቀጣዩ የቅ/ጊዮርጊስ ጨዋታ ምንም በልዩነት የምናየው ነገር የለም፡፡  ሜዳችን ላይ ነው ምንጫወተው ሜዳችን ላይ ደሞ ሪከርዳችንን አስጠብቀን ነው መቀጠል ምንፈልገው”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *