በፕሪሚየር ሊጉ መከላከያ እና ደደቢት ዛሬ ይጫወታሉ

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ምክንያት የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ ወደ ሀሙስ የተላለፈባቸው መከላከያ እና ደደቢት የ11ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ፡፡

ወላይታ ዲቻ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከተቀላቀለ ወዲህ በሜዳው የመጀመርያ የሆነውን ጨዋታ በሚያደርግበት ግጥሚያ ባለፈው እሁድ ከኮንፌድሬሽን ዋንጫ የተሰናበተውን መከላከያን በቦዲቲ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡

በ10ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን አቻ የተለያየው ወላይታ ዲቻ ያለፉትን 7 ተከታታይ ጨዋታዎች በአስገራሚ ሁኔታ በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን ዛሬ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በደጋፊዎቹ ፊት ከመከላከያ ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቀዋል፡፡ መከላከያ በበኩሉ ከድንቅ አጀማመር ቀስ በቀስ እየወረደና ከመሪውም እየራቀ እንደመምጣቱ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይህ ጨዋታ ወሳኝ ነው፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በኢትዮጵያ ዋንጫ 1ኛው ዙር ተገናኝተው በበዳሶ ሆራ ብቸኛ ግብ መከላከያ 1-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡

ይህንን ጨዋታ ተከትሎ የእለቱ ታላቅ ጨዋታ 11 ሰአት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ደደቢት መካከል ይካሄዳል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች የ10ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያላደረጉ ሲሆን በተለይም ሊጉ ከመቋረጡ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቋም ከ2 ወራት በኋላ ምን ሊመስል እንደሚችል የዛሬው ጨዋታ ይጠቁመናል፡፡

በቻምፒዮንስ ሊጉ በኬኤምኬኤም 2-0 ተሸንፎ ለጥቂት ከውድድሩ ከመውጣት የተረፈው ደደቢት ይህንን ጨዋታ አሸንፎ ቀሪዎቹን 4 ተስተካካይ ጨዋታዎች በድል የሚወጣ ከሆነ ከመሪው ያለውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ እድል ስለሚኖረው የዛሬውን ጨዋታ በትኩረት ይመለከቱታል፡፡

{jcomments on}